የሳዑዲው ግዙፉ ኩባንያ አራማኮ የኃይል ምርቱን እንደሚጨምር አስታወቀ

በእአአ 2021 የትርፍ መጠኑ በእጥፍ መጨመሩን ያስታወቀው ግዙፉ የሳዑዲ አረቢያው ኩባንያ አራማኮ፤ የኃይል ምርቱን የሚጨምር ኢንቨስትመንት ከፍ እንደሚያደርግ ይፋ አደረገ።

በሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደረው አራማኮ በቀጣይ አምስት ዓመታት የምርት መጠኑን በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር ገልጿል።

ባለፉት ጥቂት ወራት የነዳጅ እና ጋዝ ፍላጎት ከአቅርቦት መብለጡን ተከትሎ የኃይል ዋጋ ጨምሯል።

በነዳጅ እና ጋዝ ዋጋ መናር ሃሳብ የገባችው የዓለማችን መሪዎች በሳዑዲ አረቢያ ግዙፍ ኩባንያ ውሳኔ ደስተኛ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

ባለፈው ሳምንት የዩናይትድ ኪንግድም (ዩኬ) ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ወደ ሳዐዲ አረቢያ ተጉዘው አገሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ የነዳጅ ምርት ለዓለም ገበያ እንድታቀርብ ጠይቀው ነበር።

ሳዑዲ አረቢያ በነዳጅ ዘይት አምራች አገራት ድርጅት (ኦፔክ) ውስጥ ትልቋ አምራች ስትሆን፤ የምርት መጠኗን ብትጨምር በ14 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቀውን የነዳጅ ዋጋ ዝቅ ማድረግ ትችላለች።

የጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጉብኝት ግን አከራካሪ ነበር። የዩኬ ፖለቲከኞች የአገሪቱ መንግሥት የኃይል አቅርቦት ቀውስን ለመቅረፍ ከአንድ አምባገነን ወደ ሌላኛው እየሄደ ነው ይላሉ።

ሳዑዲ በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በምዕራባውያኑ ተጠያቂ ትደረጋለች። በጎረቤቷ የመን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ባላት ተሳትፎ፣ እአአ 2018 ላይ በተገደለው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ እና በሞት ቅጣት ፍርዶች በተደጋጋሚ ትወቀሳለች።

የዩኬ የፋይናንስ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኃይል አቅርቦት ዋጋን በተመለከተ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር መነጋገራቸው "ትክክል ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በዚህ አገር ውስጥ ላሉ ሰዎች ርካሽ እና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ማስገኘት የሚቻልባቸውን አማራጮች አለመመልከት ትክክል አይሆንም" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ በሳዑዲ ጉብኝታቸው ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር የሰብዓዊ መብት አያያዞችን በተመለከተም መነጋገራቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በኮቪድ-19 ወረረሽኝ ተጽእኖ ምክንያት የነዳጅ ዘይት ዋጋ ፍላጎት ቀንሶ ነበር። በዚህም እአአ 2020 ላይም የሳዑዲው አራምኮ ትርፉ ቀንሶ ነበር።

እአአ 2021 ላይ የዓለም ምጣኔ ሃብት ከወረርሸኙ ተጽእኖ ማገገም መጀመሩን ተከትሎ የኩባንያው ትርፍ ከፍተኛ ጭማሪን ማሳየት ጀምሯል።

ሳዑዲ አራምኮ በዚህ ዓመት ከ45 እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ኩባንያው ተጨማሪ ገንዘብ ወጪ ማደረጉ እአአ በ2027 13 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በቀን ማምረት እንደሚያስችለው ገልጿል። አራምኮ እአአ በ2030 የጋዝ ምርቱንም በ50 በመቶ የመጨመር እቅድ አንዳለው አስታውቋል።

ሳዑዲ አረቢያ በአሁኑ ሰዓት በቀን 10 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ታመርታለች።