ዓለም አቀፉ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ስዊፍት ምንድን ነው?

ስዊፍት የአገራት ድንበሮች ሳይገድቡት በተመቸ እና በፈጣን ሁኔታ የገንዘብ ዝውውር የሚደረግበት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ማስተላላፊያ ሥርዓት ነው።

ስዊፍት [Swift] ሶሳይቲ ፎር ኢነትረባንክ ፋይናንሻል ቴሌኮምዩኒኬሽን [Society for Worldwide Interbank Financial Telecommunication] የሚለው ስያሜ አህጽሮተ ቃል ነው። በሥርዓቱ የተካተቱ በዓለም ዙሪያ ያሉ ባንኮች ያለምንም ተጨማሪ ውጣ ውረድ ገንዘብ ይላላኩበታል።

ስዊፍት እንደ አውሮፓውያኑ በ1973 የተጀመረ ሲሆን መሰረቱ ቤልጂየም ነው። የስዊፍት ሥርዓት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ200 በላይ አገራት ውስጥ የሚገኙ 11 ሺህ ባንኮችን እና የፋይናንስ ተቋማትን አስተሳስሯል።

ስዊፍት ከመደበኛው የባንክ ሥርዓት ጋር የሚመሳሰል አይደለም። ይህ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር ክፍያዎች ሲደርሱና ሲፈጸሙ ለተጠቃሚዎች የሚያሳውቅ አጭር የጽሁፍ መልዕክት ሥርዓት ነው።

በስዊፍት ትሪሊየን ዶላሮች በኩባንያዎች እና በመንግሥታት ስለሚዘዋወር በቀን ከ40 ሚሊዮን በላይ መልዕክቶችን ይልካል። ከእነዚህ መልዕክቶች ውስጥ ሩሲያ ከአንድ በመቶ በላይ ክፍያዎችን ታስተናግዳለች ተብሎ ይታሰባል። ይህ ግን በገንዘብ ሲሰላ ቀላል የሚባል አይደለም።

ሩሲያ ከስዊፍት እንድትታገድ ጥሪ የሚቀርበው ለምንድን ነው?

በሺዎች የሚቆጠሩ ባንኮች ከሚጠቀሙበት ከዚህ የገንዘብ ማዘዋወሪያ ሥርዓት ሩሲያን ማገድ የአገሪቱን የባንክ ኔትዎርክ እና የገንዘብ አቅርቦትን ይጎዳል።

ነገር ግን ተጎጂዋ ሩሲያ ብቻ አይደለችም። ይህ ማዕቀብ የራሳቸውን ኢኮኖሚ እና ኩባንያ መልሶ እንዳይጎዳ በርካታ መንግሥታት ይሰጋሉ። ለአብነት ከሩሲያ ነዳጅ የሚቀርብላቸው አገራት በዕገዳው ምክንያት ነዳጅ ሊስተጓጎልባቸው ይችላል።

ዩናይትድ ኪንግደም ሩሲያ ከስዊፍት እንድትታገድ በአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋላስ በኩል ጥሪ ብታቀርብም ብቻዋን ልታሳካው እንደማትችል ገልጻለች። "እንዳለመታደል ሆኖ የስዊፍት ሥርዓት በእኛ ቁጥጥር ውስጥ አይደለም። በአንድ ወገን ውሳኔ የሚሳካ አይደለም" ብለዋል።

ጀርመን ሩሲያ ከስዊፍት እንዳትታገድ የማትፈልግ አገር እንደሆነች ይታማናል። በተመሳሳይ የፈረንሳይ የገንዘብ ሚኒስትር ብሩኖ ለሜሬ እና የኔዘርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩት ውሳኔው የመጨረሻ አማራጭ ብቻ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባው ጠቁመዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሩሲያን አሁን ላይ ከስዊፍ ማገድ አማራጭ ሆኖ እንዳልቀረበ ገልጸዋል። ምንም እንኳን "የተቀረው የአውሮፓ ክፍል አሁን ለመውሰድ የሚፈልገው እርምጃ ይህ ባይሆንም" አማራጭ ሆኖ እንደሚቆይ ግን ተናግረዋል።

የስዊፍትን ባለቤትና ተቆጣጣሪ ማነው?

ስዊፍት የተጀመረው አንድ ተቋም ሥርዓቱን ዘርግቶ የባንኮች የገንዘብ ዝውውር ሥርዓትን በብቸኝነት ጠቅልሎ እንዳይዝ ባቀዱ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ባንኮች አማካይነት ነው። ሥርዓቱን ከ2,000 የሚልቁ ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት በጋራ ባለቤትነት ይዘውታል።

ይህ የስዊፍት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት በቤልጂየም ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር የሚደረግበት ሲሆን የአሜሪካ ፌዴራል ግምጃ ቤትን እና የእንግሊዝ ባንክን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ ዋና ዋና ማዕከላዊ ባንኮችም በቁጥጥሩ ይሳተፋሉ።

ስዊፍት በአባል አገራት መካከል ደኅንነቱ የተጠበቀ ዓለም አቀፍ ንግድ እንዲኖር የሚረዳ ሲሆን ግጭቶች ሲኖሩ ለማንም እንዳይወግን ይጠበቃል።

ሆኖም ከዚህ መርኅ በተቃራኒ ኢራን በኒውክሌር መርሃ ግብሯ ላይ በተጣለባት ማዕቀብ ምክንያት እንደ አውሮፓውያኑ በ2012 ከስዊፍት ታገደች። በዚህም ምክንያት ወደ ውጭ ከምትልከው የነዳጅ ሽያጭ ገቢዋ ግማሹን ያጣች ሲሆን 30 በመቶ የውጭ ንግዷንም አጥታለች።

ስዊፍት ግን ማዕቀቡ እንዲጣል ምንም አይነት ተጽእኖ እንዳላደረገ እና ውሳኔው በመንግሥታቱ ላይ የተመሰረተ ነው ብሏል።

ሩሲያን ከስዊፍት ማገድ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?

ሩሲያ ከስዊፍት ሥስርዓት ከታገደች የአገሪቱ ኩባንያዎች በስዊፍት በኩል የሚያገኙት መደበኛ፣ የተመቸ እና ፈጣን የገንዘብ ልውውጥን ያጣሉ። በተጨማሪም ለኃይል አቅርቦት እና ለእርሻ ምርቶች ክፍያዎች የሚፈጸምበት መንገድ ክፉኛ ይስተጓጎላል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ሩሲያ ክሪሚያን መውረሯን ተከትሎ ከስዊፍት ልትታገድ እንደምትችል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷት ነበር። ሩሲያ እርምጃውን ጦርነት ከማወጅ አሳንሳ እንደማትመለከተው አሳውቃ ነበር።

በወቅቱም ምዕራባውያኑ በውሳኔው ባይገፉበትም ሩሲያ ግን የራሷን ተመሳሳት ሥርዓት እንድትፈጥር አጋጣሚ የፈጠረላት ነበር።

እንዲህ ያለውን ማዕቀብ ለመቋቋም የሩሲያ መንግሥት ለካርድ ክፍያዎች የሚሆን 'ሚር' የተሰኘ ብሔራዊ የክፍያ ካርድ ሥርዓት ዘርግቷል። ነገር ግን ጥቅም ላይ የዋለው በጥቂት አገራት ውስጥ ብቻ ነው።

ምዕራቡ በስዊፍት ላይ ለምን ተከፋፈለ?

ሩሲያን በስዊፍት እንዳትጠቀም ማገድ ከአገሪቱ ጋር የንግድ ልውውጥ ያላቸውን ወይም ምርት የሚያቀርቡ እና የሚገዙ ኩባንያዎችን ይጎዳል። በተለይም ጀርመን የመጀመሪያዋ ተጎጂ ትሆናለች።

ሩሲያ የአውሮፓ ሕብረት የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ዋነኛ አቅራቢ ስትሆን፣ ለሕበረቱ አማራጭ አቅርቦቶችን ማግኘት ቀላል አይሆንም። የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በዚህ ሳቢያ መሰል ችግር እንዲፈጠር መንግሥታቱ አይፈልጉም።

እንዲሁም በሩሲያ ዕዳ ያለባቸው ኩባንያዎች ክፍያ የሚያገኙበት አማራጭ መንገዶችን መፈለግ ግድ ይላቸዋል። የሩሲያ ከስዊፍት መውጣት የዓለም አቀፍ የባንክ ሥርዓት ላይ የሚፈጥረው ቀውስ ቀላል እንዳሆነ ይታመናል።

የሩሲያ የቀድሞ የፋይናንስ ሚኒስትር አሌክሲ ኩድሪን የአገሪቱ ስዊፍት መታገድ ምጣኔ ሀብቷን በ5 በመቶ እንዲያሽቆለቁል ሊያደርገው ይችላል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ውሳኔው በሩሲያ ኢኮኖሚ ላይ ዘላቂ ተጽእኖ ስለማምጣቱ አጠራጣሪ ነው። ምክንያቱም የሩሲያ ባንኮች የራሷ የክፍያ ሥርዓት ያላት ቻይናን ጨምሮ በሌሎች ማዕቀብ ባልጣሉ አገሮች በኩል የመጠቀም እድል ስላላቸው ነው።

ሩሲያ ስዊፍት እንድትታገድ የአሜሪካ የሕግ አውጪዎች ግፊት እያደረጉ ነው። ሆኖም ፕሬዝዳንት ባይደን ምርጫቸው ይህ ሳይሆን ሌሎች ማዕቀቦች ናቸው። ምክንያቱም ውሳኔው ሌሎች አገራትን እና ምጣኔ ሀብታቸውን ስለሚጎዳ ነው።

እናም ሩሲያ ከዚህ ሥርዓት እንድትታገድ የአውሮፓ አገራትን ድጋፋ ይፈልጋል። አገራቱ ደግሞ ውሳኔው ራሳቸውን መልሶ የሚጎዳ በመሆኑ ብዙም ሊደፍሩት የሚፈልጉ አይመስሉም።