ሩሲያ እና ዩክሬን: አዲሱ የገንዘብ ዝውውር ማዕቀብ ሩሲያን ምን ያህል ይጎዳታል?

በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የተለያዩ ከባድ ማዕቀቦችን እየጣሉባት ነው።

የሩሲያ ባንኮችን ስዊፍት ከተሰኘው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት መታገዳቸው እና የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ዓለም አቀፍ የባንክ ተግባር እንያከናውን የተጣለበት ማዕቀብ ግን የመጨረሻው እና የከፋው ነው።

የሩሲያ ባንኮች ከስዊፍት ዓለም አቀፉ የክፍያ ሥርዓት መገለላቸው በሩሲያ የሚገኙ የገንዘብ ተቋማት እና በሌሎች ኩባንያዎች ላይ በፈጥነት የሚታይ ወይም እያደር የሚገለጥ ጫና ይዞ ይመጣል።

ከስዊፍት መታገደ በሩሲያ የተጀመረ አይደለም። እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 አሜሪካ የኢራን ባንኮችን ከስዊፍት ሥርዓት ለማስገለል ችላለች።

የኢራን ኢኮኖሚ ከሩሲያ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ቢሆንም ይህንን እርምጃ በወቅቱ በርካታ የአውሮፓ መንግሥታት ተቃመውት ነበር።

ሁለት ሦስተኛ የሚሆነውን የነዳጅ አቅርቦቷን ከሩሲያ የምታገኘው ጀርመን ጉዳዩ በተለየ ሁኔታ አስጨንቋታል። ከሩሲያ ወደ ጀርመን የተዘረጋው ነዳጅ ማስተለለፊያ ፈቃድም በጀርመን ታግዷል።

ጉዳዩ በዝርዝር ባይታወቅም የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት ከሩሲያ ባንኮች ጋር ግንኙነት ያሏቸው ተቋሞቻቸው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ምንም እንኳን እቀባው ሩሲያን የሚፈትን ቢሆንም አማራጭ ግን የላትም ማለት አይደለም። እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ሩሲያ ክሬሚያን ከወረረች በኋላ ይፋ ያደረገችው ኤስ ፒ ኤፍ ኤስ ወይም የፋይናንሺያል መልዕክቶች ማስተላለፊያ ሥርዓት የሚባል አማራጭ አላት።

ተመሳሳይ ሥርዓት ቻይናም ዘርግታለች። ቻይና ድንበር ተሻጋሪ ሲ አይ ፒ ኤስ የሚባል ተጨማሪያ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት አላት።

ታዲያ ሩሲያ ላይ የወረደው ይህ ማዕቀብ ለቻይና መልካም አጋጣሚ ሳይፈጥር አልቀረም። ሩሲያ አማራጭ ፍለጋ ወደ ቻይና መጠጋቷ አይቀርም።

ይህ ደግሞ የአሜሪካ ዶላርን መሰረት ያደረገ የፋይናንሺያል የበላይነቱን ለመናድ ለሚታትረው የፕሬዝዳንት ዢ አስተዳደር ያልተጠበቀ በር ከፍቷል። ሃሳቡንም በፍጥነት ወደ ተግባር ለመቀየር ያግዛል።

ሆኖም ቻይና ከሌላው ዓለም ጋር ያላት የገቢና የወጪ ንግድ ግንኙነት በጣም ትልቅ በመሆኑ፣ ቻይና በዚህ ፍጥነት ሩሲያን ለመርዳት ፈቃደኛ ላትሆን ትችላለች የሚሉም አሉ።

ለሩሲያን ከስዊፍት ከመገለል የበለጠ ጉዳት የሚያመጣባት የሩሲያን ማዕከላዊ ባንክ ሥራን ለማቀብ የሚወሰደው እርምጃ ነው።

630 ቢሊየን ዶላር ዓለም አቀፋዊ የዶላር ክምችቷን እንዳትጠቀም መከልከል በሩሲያ ኢኮኖሚ ላይ አስከፊ ምት ማስከተሉ ሳይታለም የተፈታ ነው።

ሌላው የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ለሩሲያ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ከዚህ በኋላ የተለሳለሰ አቋም አይኖረኝም ብሏል።