ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምዕራባውያን በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ ላይ ማዕቀብ ጣሉ
በዩክሬን ላይ በተፈጸመው ወረራ ምክንያት ምዕራባውያን አገራት በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ ላይ የተለየ ማዕቀብ ጣሉ።
በዚህም መሠረት በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ሕብረት፣ በዩናይትድ ኪንግደምና በካናዳ ያለ የሁለቱ የሩሲያ ከፍተኛ መሪዎች ሐብት እንዳይንቀሳቀስ የተጋደ ሲሆን፣ አሜሪካ ደግሞ የጉዞ እገዳ ጥላባቸዋለች።
በመሪዎች ላይ እንዲህ ያለውን ማዕቀብ መጣል ብዙም የተለመደ አይደለም። የአውሮፓ ሕብረት ከዚህ በፊት ተመሳሳይ እርምጃ ወስዶ የሚያውቀው በሶሪያ እና በቤላሩስ ፕሬዝዳንቶች ላይ ብቻ ነበር።
አሜሪካ ደግሞ ተመሳሳይ እርምጃ የወሰደችው በቬንዙዌላው መሪ ኒኮላስማዱሮ እና በሶሪያው ባሻር አል አሳድ ላይ ነው።
ፕሬዝዳንት ፑቲንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ በተለያዩ የምዕራብ አገራት ውስጥ ያላቸው ንብረት ምን ያህል እንደሆነ የማይታወቅ ሲሆን የተጣለው ዕቀባም የሚኖረው ውጤት ግልጽ አይደለም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ደግሞ በዩክሬን ላይ የተፈጸመውን ወረራ ለማውገዝ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ሩሲያ ድምጽን በድምጽ በመሻር መብቷ ውድቅ አድርጋዋለች።
ወረራውን ለማውገዝ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ሩሲያ ውድቅ ስታደርገው ከ15ቱ የፀጥታው ምክር ቤቱ አባላት አስራ አንዱ ደግፈውታል፤ ሕንድ፣ቻይናና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ድምጻቸውን ሰጥተዋል።
ሩሲያ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባልና ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ካላቸው አምስት አገራት አንዷ በመሆኗ የውሳኔ ሐሳቡ ለምክር ቤቱ ሲቀርብ ከመነሻው ተቀባይነት እንደማያገኝ ይታወቅ ነበር።
በፕሬዝደንቱ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ላይ ምዕራባውያን የጣሉት ማዕቀብ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ በፈጸመች በሁለተኛው ቀን ላይ ሲሆን፣ ውጊያው ወደ ዋና ከተማዋ ደርሶ የጎዳና ላይ ውጊያ እየተካሄደ ነው።
ምዕራባውያን በዩክሬን ላይ ለተፈጸመው ወረራና ከሚከተለው ደም መፋሰስ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ተጠያቂ ሲያደርጉ፣ ፕሬዝዳንቱ ግን አገራቸው ይህንን እርምጃ የወሰደችው ምሥራቅ ዩክሬን ያሉ ሰለማዊ ሰዎችን ለመከላከል እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ከአሜሪካ ተለይቶ ለጊዜው የጉዞ እገዳን በሩሲያ መሪዎች ላይ ከመጣል ተቆጥቧል።
የሩሲያ ወታደሮች ወደ ዋና ከተማዋ ኪዬቭ እየተቃረቡ በነበረበት ጊዜ የዩክሬን መሪዎች ሩሲያ ለፈጸመችው ወረራ መቀጣጫ ጠንካራ ማዕቀብ በምዕራባውያን እንዲጣል ሲጠይቁ ነበር።
ምዕራባውያን ሩሲያ ለወሰደችው እርምጃ አጸፋ ወታደራዊ ዘመቻ እንደማያካሂዱ በተለያዩ መንገዶች የገለጹ ሲሆን፣ ነገር ግን በሁሉም በኩል በሩሲያ ላይ ከባድ ጫናን የሚያሳርፍ ማዕቀብ ለመጣል ዝተዋል።
እስካሁን አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ምዕራባውያን የተለያዩ እርምጀዎችን በተናጠልና በጋራ የወሰዱ ሲሆን ወረራው የሚቀጥል ከሆነ ማዕቀብና እገዳዎች በተከታታይ ይቀጥላሉ እየተባለ ነው።