ሩሲያ እና ዩክሬን: በሩሲያ ወረራ የተፈጸመባት ዩክሬን መሪ ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ማን ናቸው?

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ለመጀመሪያ ጊዜ ቴሌቪዥን ላይ ሲቀርቡ በአንድ ታዋቂ አስቂኝ ተከታታይ ድራማ ላይ ፕሬዝዳንት ሆነው ነበር።

ነገር ግን 2019 ላይ በትወናው የተሳካለቸው ዜሌንስኪ የፕሬዝዳንትነት መንበር ላይ ወጥተው የምር ሆነ። አሁን የ44 ሚሊዮን ዩክሬናውያን መሪ ሲሆኑ በሁሉም የድንበር አካባቢዎች ደግሞ በሩሲያ በኩል ከባድ አደጋ ተጋርጦባቸዋል።

በተከታታይ ድራማው ላይ ዜሌንስኪ የሚጫወቱት ትሁቱ የታሪክ መምህር ገጸ ባህሪይ በአገሪቱ ያለውን ሙስና በመቃወም ባስተላለፈው የተንቀሳቃሽ መልዕክት አማካይነት ታዋቂ ይሆናል። ትንሽ ቆይቶም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆኖ ወደ መሪነት መንበር ላይ ይወጣል። ታዲያ ዩክሬናውያን ይህንን ድራማ እውን ብናደርገውስ ያሉ ይመስላል።

ቮሎድሜር ዜሌንስኪ የምርጫ ቅስቀሳቸውን በሚያደርጉበት ወቅት የሕዝቡ አገልጋይ ወደ ሥልጣን ሊመጣ ነው እያሉ ደጋፊያቸውን ማብዛት ችለዋል።

አሁን የሩሲያ ወታደሮች የዩክሬንን ድንበር ጥሰው በመግባት ወደ ዋና ከተማዋ ደርሰዋል። ታዲያ በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ አገሪቱን የማረጋጋትና ወታደሩን የማስተባበር እንዲሁም አገርን የመጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት እምብዛም ፖለቲካዊ ልምድ በሌላቸው ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጫንቃ ላይ ወድቋል።

የ44 ዓመቱ ፕሬዝዳንት በአገር ውስጥ ረብሻ እንዳይፈጠርና ሕዝቡን ለማረጋጋት እየጣሩ በጎን ደግሞ የምዕራቡ ዓለም ወዳጆቻቸው የእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉላቸው እየተማጸኑ ነው።

ክሪቪ ሪህ በተባለችው ትልቅ ከተማ ከአይሁዳውያን ቤተሰቦች የተወለዱት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ፣ ከኪዬቭ ብሔራዊ ኢኮኖሚክስ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። ነገር ግን አስቂኝ ትወናዎችን መስራት የነፍስ ጥሪያቸው ሆነ።

በወጣትነታቸው በሩሲያ ቴሌቪዥን ይተላለፍ የነበረ የኮሜዲ ውድድር ላይ በተደጋጋሚ ተሳትፈዋል። እአአ 2003 ላይ ደግሞ 'ክቫርታል 95' የተሰኘ የቴሌቪዥን ዝግጅቶች አዘጋጅ ድርጅት በመክፈት ትልቅ ስኬትን ማግኘት ችለዋል።

የዚህ ድርጅት መስራቾቹ ሁለት ሰዎች ናቸው። ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ እና ቢሊየነሩ ኢሆር ኮሎሞስኪ። መጨረሻ ላይ ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ፕሬዝዳንት ለመሆን ሲወዳደሩ እኚህ ግለሰብ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውላቸዋል።

ዜሌንስኪ ወደ ፖለቲካው ዓለም የተቀላቀሉት በአውሮፓውያኑ 2014 ላይ በዩክሬን ተቀስቅሶ በነበረው ሕዝባዊ አመጽ አማካይነት ነበረ።

ያ ወቅትም በሩሲያ የሚደገፉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች ከወራት ተቃውሞ በኋላ ከሥልጣናቸው የተባረሩበት ነበር። በመቀጠል ሩሲያ ክሪሚያን ተቆጣጥራ የግሏ አደረገችና በስተምሥራቅ በኩል አማጺያንን መደገፍ ያዘች።

ከአንድ ዓመት በኋላ ጥቅምት 2015 ላይ 'ሰርቫንት ኦፍ ዘ ፒፕል' ወይንም 'የሕዝቡ አገልጋይ' የተሰኘው ዜሌንስኪ የሚተውኑበት ተከታታይ ድራማ ለሕዝብ እይታ ቀረበ። በርካታ ዩክሬናውያንም እንዲህ አይነት መሪ ነው የሚያስፈልገን ብለው አመኑ።

በቀጣይ በተካሄደውም ምርጫ ዜሌንስኪ አሸንፈው የምርም ፕሬዝዳንት ሆኑ። በወቅቱ ተፎካካሪያቸው የነበሩት ፕሬዝዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ፣ ዜሌንስኪ 'በፖለቲካው ዓለም ምንም ልምድ የሌላቸውና የማይመጥኑ ናቸው' ብለው ቢወርፏቸውም በስተመጨረሻ ግን አሸናፊ መሆን ችለዋል።

ዩክሬናውያንም 73.2 በመቶ ድምጽቻውን ለቮሎድሚር ዜሌንስኪ በመስጠት 2019 የአገሪቱ ስድስተኛ ፕሬዝዳንት አድርገዋቸዋል።

በምሥራቃዊ ዩክሬን የተቀሰቀሰውን ግጭት ፕሬዝዳንቱ ለማረጋጋት የቻሉትን ያህል ቢጥሩም እስካሁን እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ማምጣት አልቻሉም። በዚህ ግጭት ምክንያት ብቻ ከ14 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ ይነገራል።

መጀመሪያ ላይ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ከሩሲያ ጋር ድርድርን ነበር የመረጡት። በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ንግግሮች እንዲሁም የእስረኛ ልውውጥ ሁሉ እስከማድረግ ደርሰዋል።ነገር ግን አሁንም ዘላቂነት ያለው መፍትሄ ማግኘት አልተቻለም።

ቭላድሚር ፑቲን ግጭቱ በሚካሄድባቸው ምሥራቃዊ የዩክሬን ግዛቶች ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች የሩሲያ ፓስፖርት መስጠት መጀመራቸው ደግሞ ነገሮችን አባብሷል።

በሌላ በኩል ከሁለት ዓመት በፊት የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነትም ቢሆን አልፎ አልፎ በሚደረጉ የተኩስ ልውውጦች ምክንያት ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል።

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ዩክሬን የአውሮፓ ሕብረት አባል አገር እንድትሆንና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ኔቶ አባልም እንድትሆን ይፈልጋሉ፤ በርካታ ሥራዎችንም አከናውነዋል።

ምዕራባዊያን፤ ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን አገሮች [ኔቶ] አባል እንደትሆን ሊፈቀድላት አይገባም የሚለውን የሩሲያን ሐሳብ ውድቅ አድርገው አዳዲስ አባላት መግባት አለባቸው በማለት ፍጥጫ ውስጥ ቆይተዋል።

ሩሲያ ደግሞ በድንበር አካባቢ ወታደር ያሰባሰብኩት ለራሴው ደኅንነት በመስጋት ነው፤ ዩክሬን የኔቶ አባል አገር የምትሆነ ከሆነ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የደኅንነት ስጋት ይፈጥርብኛል በማለት ይህንን ሀሳብ አምርራ ትቃወማለች።

የሩሲያ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ኔቶን ስለመቀላቀል ሀሳባቸውን ያስቀይራቸው እንደሆነ የተጠየቁት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚየር ዜሌኒስኪ "ለእኔ ትልቁ ነገር አገሬን ማስቀጠል ነው። ኔቶ ዝም ብሎ ቃል አይደለም። ኔቶ የደኅንነት ማረጋገጫ መንገድ ነው'' ብለው ነበር።

ነገር ግን ሩሲያ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን በማስገባት ወረራ ከፈጸመች ሦስተኛ ቀኗ ቢሆንም ምዕራባውያንና የኔቶ አባላት ጠንካራ ማዕቀቦችን በሩሲያና በመሪዎቿ ላይ ከመጣል ውጪ፣ ዩክሬንን ለመታደግ አስካሁን የወሰዱት እርምጃ የለም።

ፕሬዝዳንት ዜሌኒስኪ ያቀረቡት የተኩስ አቁም ንግግር ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ "አገራችንን መከላከላችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

ዜሌኒስኪ "ምዕራባውያኑ ሁኔታውን ከሩቅ ሆነው መመልከትን መርጠዋል" ካሉ በኋላ "እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም አገራችንን ለብቻችን እየተከላከልን ነን" በማለት ምዕራባውያን ለዩክሬን ድጋፍ እንዲሰጡ ዳግም ጠይቀዋል።

ዩክሬን በምሥራቅ ያለውን ጦርነት ካላቆመች ለሚኖረው ደም መፋሰስ ተጠያቂ እንደምትሆን ፕሬዝዳንት ፑቲን አስጠንቅቀዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ሐሙስ ምሽት ላይ ባደረጉት ንግግር ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመነጋገር ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱን አስታውቀዋል።

"ከሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጋር የስልክ ንግግር ለማድረግ ሞከርኩ። ውጤቱ ዝምታ ሆነ" ብለዋል ዜሌንስኪ።

ሩሲያ ወደ 200 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች እና በሺዎች የሚቆጠሩ የውጊያ መኪናዎች በዩክሬን ድንበር እንዳሏት ተናግረዋል።

ዜሌንስኪ ንግግራቸውን ከዩክሬን ቋንቋ ወደ ሩስኪ በመቀየር ሩሲያውያን በዩክሬን ጉዳይ እየተዋሹ መሆኑን ጠቅሰው ጥቃትን እንዲቃወሙ በስሜት ተሞልተው ተማፅነዋል።

የዩክሬኑ መሪ አገራቸው ለሩሲያ ጥቃት ዝግጁ መሆኗን ተናግረው "እነሱ [ሩሲያ] ጥቃት ካደረሱ፤ አገራችንን፣ ነፃነታችንን፣ ሕይወታችንን፣ የልጆቻችንን ሕይወት ሊወስዱ ከሞከሩ ራሳችንን እንከላከላለን" ሲሉ ቃል ገብተዋል።