የዩክሬን ወረራ፡ ሩሲያ በፌስቡክ አጠቃቀም ላይ ገደብ ጣለች

ሩሲያ ዩክሬንን በወረረችበት በዚህ ወቅት ፌስቡክ በሞስኮ ከሚደገፉ የዜና አውታሮች አንጻር በያዘው አቋም ምክንያት በማኅበራዊ መድረኩ አጠቃቀም ላይ ገደብ ጣለች።

የሩሲያ ኮሙኒኬሽን ተቆጣጣሪ ሮስኮምናድዞር ማኅበራዊ መድረኩ "ሳንሱር የሚያደርግና የሩሲያ ዜጎችን መብትና ነጻነት የሚጥስ ነው" ብለዋል።

ፌስቡክ በበኩሉ በመንግሥት ባለቤትነት ሥር ከሚገኙ የዜና ድርጅቶች የወጡ መረጃዎችን መፈተሽ እና ይዘቱን ማጣራቱን እንዲሁም መለየቱን ለማቆም ፈቃደኛ አለመሆኑን ገልጿል።

ይህ ውሳኔ የተሰማው ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈፀመች ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

ይሁን እንጂ የቁጥጥር ገደቡ ምን እንደሆነ እና የፌስቡክ ባለቤት ኩባንያ [ሜታ] ሌሎች የማኅበራዊ መድረኮች የሆኑት ዋትስአፕ፣ ፌስቡክ ሜሴንጀር እና ኢንስታግራም ውሳኔው ይነካቸው እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

ተቆጣጣሪው እንዳለው ፌስቡክ ሐሙስ ዕለት የመንግሥት የዜና ወኪል የሆኑት አርአይኤ፣ የመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ ዝቬዝዳ እና ክሬምሊንን የሚደግፉ የዜና ገጾች 'ሌንታ ዶት አርዩ' እና 'ጋዜታ ዶት አርዩ' ላይ ያስቀመጠውን ገደብ እንዲያነሳ ጠይቋል።

ነገር ግን ሜታ ይህንን ጥያቄ "ችላ ብሎታል" ብሏል ተቆጣጣሪው።

በሜታ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት የሆኑት ኒክ ክሌግ በበኩላቸው "የሩሲያ ባለሥልጣናት በዜና አውታሮቹ የሚወጡ ይዘቶችን ገለልተኛ የሆነውን የመረጃ ማጣራት እና መለየት ሥራ እንድናቆም አዘውናል፤ ይህንንም አልተቀበልንም" ብለዋል።

ነገር ግን ምክትል ፕሬዚደንቱ ሩሲያውያን የሜታን ማኅበራዊ መድረኮች መጠቀማቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ተራ የሩሲያ ዜጎች ራሳቸውን ለመግለጽና ለተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመደራጀት መተግበሪያዎቻችንን እየተጠቀሙ ነው" ያሉት ኒክ፤ ኩባንያው እነዚህ ዜጎች ድምጻቸውን ማሰማታቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚፈልግም አስረድተዋል።

በሩሲያ የሚገኙ በርካታ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ወረራውን "ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን" በማለት የሩሲያ ጦር ወደ ዩክሬን መቃረቡን አዎንታዊ ምሥል አላብሰውታል።

ሐሙስ ዕለት ሜታ በዩክሬን ያለውን ግጭት በተመለከተ የሚወጡ ይዘቶችን ለመቆጣጠርና ለመከታተል "ልዩ የሆነ የኦፕሬሽን ማዕከል" ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

ሩሲያ ከፌስቡክ ጋር የሚወዳደር ቪኬ እና ኦድኖክላስኒኪ የተባሉ የራሷ ማኅበራዊ መድረክ አላት። ይሁን እንጂ ሜታ የሚያስተዳድራቸው ፌስቡክና ኢንስታግራምም በአገሪቷ በስፋት ይታወቃሉ።

አርብ ዕለት የአሜሪካ ሴናተር ማርክ ዋርነር ፌስቡክ ፣ ዩቲዩብ እና ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎቶች ላይ "የሚጻፉ ነገሮች የሰብአዊ መብት ረገጣን ለማመቻቸት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የማረጋገጥ ግልጽ ኃላፊነት አለባቸው" ብለዋል።

ሜታ የተሳሳተ መረጃዎችን ለመለየት በሚያደርገው ጥረት የተለያዩ ጫናዎች ሲደረጉበት ቆይቷል። ይህንንም ለመፍታት ሮይተርስን ጨምሮ ከኩባንያው ውጭ ከሆኑ የመረጃ አረጋጋጮች ጋር እየሠራ ነው።

ሞስኮ ዩክሬንን መውረሯን በሚመለከት "ሐሰተኛ መረጃ" በማለት የገለጸቻቸውን ዘገባዎች እንዲያቆሙ በማስፈራራት በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ላይ ጫናዋን ጨምራለች።

ትዊተር በበኩሉ የደኅንነት ቡድኖቹ "ሐሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎችን ለማጉላት የተደረጉ ሙከራዎችን እየተከላከሉ ነው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።