ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምዕራባውያን በሩሲያ እና በፑቲን ላይ ምን አይነት ማዕቀቦችን ሊጥሉ ይችላሉ?
ምዕራባውያን አገራት ሩሲያ ዩክሬንን የምትወር ከሆነ በርካታ ማዕቀቦችን ሊጥሉባት እንደሚችሉ እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።
ኃያላኑ ምዕራባውያን በሩሲያ እና በመሪያዋ ቭላድሚር ፑቲን ላይ ሊጥሉ የሚችሏቸው የማዕቀብ አይቶችን ይፋ ባያደርጉም፤ ተንታኞች ግን የሚከተሉት ማዕቀቦች በሞስኮ እና ፑቲን ላይ ሊተገበሩ ይችላሉ እያሉ ነው።
የገንዘብ ዝውውር ዕቀባዎች
በሩሲያ ላይ ሊጣሉ ከሚችሉ ማዕቀቦች መካከል አንዱ ሞስኮን 'ስዊፍት' ከተባለው የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ማገድ ነው።
ስዊፍት ከ200 በላይ በሆኑ አገራት፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ኩባንያዎች የፋይናንስ መልዕክቶችን ለመለዋወጥ የሚጠቀሙት የየገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ነው።
ሩሲያ ከስዊፍት ታገደች ማለት፤ ባንኮቿ ከአገር ውጪ ካሉ ባንኮች ጋር የገንዘብ ዝውውር ማድረግ በእጅጉን አዳጋች ያደርግባቸዋል።
መሰል ማዕቀብ እአአ 2012 ላይ ኢራን ላይ ተጥሎ ነበር። ታዲያ ኢራን በዚህ ማዕቀብ ምክንያት ከነዳጅ ገበያ ማግኘት የነበረባትን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሳትሰበስብ ቀርታለች።
የዶላር ክልከላ
ዋሽንግተን ሞስኮ የአሜሪካ ዶላርን ለግብይት እንዳትጠቀም መከልከል ትችላለች።
ሩሲያ ዶላርን መጠቀም አትችልም ከተባለች፤ በምዕራባውያን አገራት የሚገኙ ባንኮች ከሩሲያ ባንኮች ጋር በዶላር ልውውጥ ቢያደርጉ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
ይህ ደግሞ ሩሲያ ከተቀረው ዓለም ጋር የሚኖራት ግብይት እጅጉን የተገደበ ይሆናል። ሩሲያ የጋዝ አቅርቦቷ ለገበያ የሚቀርበው በአሜሪካ ዶላር እንደመሆኑ በምጣኔ ሃብቷ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍ ያለ ነው።
የባንክ እገዳዎች
አሜሪካ በቀላሉ የሩሲያ ባንኮችን ጥቁር መዝገብ ላይ ልታሰፍር ትችላለች። ይህ ማለት ማንኛውም አካል ከሩሲያ ባንኮች ጋር ግብይት መፈጸም ፍጹም እንዳይቻለው እንደማድረግ ይቆጠራል።
ይህ በሞስኮ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት ያደርጋል።
አሜሪካ በሩሲያ ባንኮች ላይ የምትጥለው እገዳ ጉዳቱ ለሞስኮ ብቻ አይተርፍም። ገንዘባቸው በሩሲያ ባንኮች ያስቀመጡ ምዕራባውያን ዲታዎችም የዚህ ገፈት ቀማሽ ይሆናሉ።
የኤክስፖርት ቁጥጥር ገደቦች
ምዕራባውያኑ ሩሲያ ምን፤ በምን ያክል መጠን ወደ አገር ውስጥ ታስገባ የሚለውን መቆጣጠር ይችላሉ።
ለምሳሌ አሜሪካ ኩባንያዎቿ የአሜሪካ ቴክኖሎጂ ወይም ሶፍትዌር ውጤት የሆኑ ምርቶች በሩሲያ ገበያዎች ላይ እንዳይሸጡ ልታግድ ትችላለች።
የኃይል ሽያጭ ገደብ
የሩሲያ ምጣኔ ሃብት መሠረቱን ካደረገባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የጋዝ እና የነዳጅ ሽያጭ ላይ ነው። ክሬምሊን ለምዕራባውያኑ ጋዝ እየሸጠች ከፍተኛ ገንዘብ ታገኛለች።
ምዕራባውያኑ አገራት እና ኩባንያዎች ከሩሲያ ጋዝ እና ነዳጅ መግዛትን መከልከል ይችላሉ።
ይህ ውሳኔ በተመሳሳይ በተለይ ለአውሮፓውያኑ አገራት ከባድ ኪሳራን ይዞ ሊመጣ ይችላል።
አውሮፓውያኑ በብዛት የሚጠቀሙት ጋዝ ምንጩ ከሩሲያ እንደመሆኑ፤ በሩሲያ የኃይል አቅርቦት ላይ ዕቀባ ቢጣል በአውሮፓ የጋዝ ዋጋ ጣራ ይነካል።
ግለሰቦችን ዒላማ ማድረግ
አዳዲስ ማዕቀቦች ግለቦች ላይ ሊጣሉ ይችላሉ። ይህ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቅርብ አጋሮቻቸውን ሊጨምር ይችላል።
የንብረት እና የጉዞ እገዳ ደግሞ ዋነኛዎቹ ግለሰቦች ላይ ሊጣሉ የሚችሉ ማዕቀቦች ናቸው።
በተጽኖ ፈጣሪ ሩሲያውያን ላይ መሰል ማዕቀብ መጠል ምናልባት ንብረታቸውን እና አራሳቸውን ማንቀሳቀስ ያልቻሉ ግለቦች ፕሬዝደንት ፑቲን ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ የሚል ግምት በምዕራባውያን አገራት መንግሥታት ዘንድ ሊፈጠር ይችላል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለምዕራባውያኑ በቀላሉ የማይመለሰው ጥያቄ በሩሲያ ላይ መቼ እና ምን አይነት ማዕቀብ መጣል አለበት የሚለው ነው። ምዕራባውያን አገራትም በዚህ ላይ የተለያየ አቋም ሊያንጸባርቁ ይችላሉ።