ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጄኔራል ባጫ እና ኢንጂነር ስለሺን ጨምሮ ለ27 ግለሰቦች የአምባሳደርነት ሹመት ተሰጠ
ጄኔራል ባጫ ደበሌ፣ ጄኔራል ሃሰን ኢብራሂምና፣ ኢንጂነር ስለሺ በቀለን ጨምሮ ለ27 አምባሳደሮች ሹመት መሰጠቱን የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የአምባሳደርነት ሹመት የሰጡት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በዛሬው ዕለት ጥር 18/2014 ዓ.ም መሆኑም ተገልጿል።
ከፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጽህፈት ቤት የወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው ፕሬዚዳንቷ የሰጡት ሹመት ለ16 ግለሰቦች የባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እንዲሁም ለሌሎች 11 ግለሰቦች ደግሞ የአምባሳደርነት ሹመቶች ናቸው።
በሙሉ አምባሳደርነት ከተሾሙት ውስጥ በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ጋር ተያይዞ ስማቸው የሚነሳው የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ጦር ጄኔሎቹ ጄኔራል ባጫ ደበሌ እና ጄኔራል ሃሰን ኢብራሂም ተካትተውበታል።
ጄኔራል ባጫ ደበሌ ወደ ጦሩ እንደገና እንዲካተቱ የተደረጉት የትግራይ ጦርነት በተቀሰቀበት ዕለት ነበር።
በቅርቡም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቅራቢነት በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የጄነራል ማዕረግ ከተሰጣቸው ወታደራዊ መኮንኖች መካከል አንዱ የነበሩትና በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ የሆኑት ጄነራል ባጫ ደበሌ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙ ሲሆን የሚላኩበት አገር እስካሁን አልተገለጸም።
እንዲሁም የቀድሞው የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትር፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሚኒስትር ማዕረግ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና የሕዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪና አማካሪ ሆነው እያገለገሉ ያሉት ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለም ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ ሲያገለግሉ የቆዩ በአጠቃላይ 27 ሰዎች በባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነትና በአምባሳደርነት ሹመት ተሰጥቷቸዋል።
በባለሙሉ ባለስልጣን አምባሳደርነት የተሾሙት ግለሰቦች
- ጀነራል ባጫ ደበሌ
- ጀነራል ሀሰን ኢብራሒም
- ዶክተር ስለሺ በቀለ
- አቶ ተፈራ ደርበው
- አቶ ደሴ ዳልኬ
- ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ
- ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ
- አቶ ረሻድ መሀመድ
- አምባሳደር ጀማል በከር
- አቶ ፈይሰል አሊይ
- አቶ ኢሳያስ ጎታ
- አቶ ጸገአብ ክበበው
- አቶ ጣፋ ቱሉ
- ዶክተር ገነት ተሾመ
- አቶ ዳባ ደበሌ እና
- አቶ ፈቃዱ በየነ
በአምባሳደርነት የተሾሙት ግለሰቦች
- አቶ አሳዬ አለማየሁ
- አቶ ሃይላይ ብርሃነ
- አቶ አወል ወግሪስ
- ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት
- አቶ አንተነህ ታሪኩ
- አቶ አክሊሉ ከበደ
- አቶ ሰይድ መሐመድ
- አቶ ዮሴፍ ካሳዬ
- አቶ ዘላለም ብርሃን
- ወይዘሮ ፍርቱና ዲባኮ
- አቶ ወርቃለማሁ ደስታ