ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ግድቡ የእኔ ነው" አባባልን የፈጠሩት የቀድሞው የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ
በአዲሱ ካቢኔ ያልተካተቱት የቀድሞው የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ "በቀጣይ አገሬ በምትፈልገኝ አገልግሎት የምሰማራ ይሆናል" ሲሉ በማኅበራዊ ድረ ገጾቻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ከውሃ ሙሌቱ እንዲሁም በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስለ ግድቡ ከተካሄዱ ውይይቶች ጋር በተያያዘ ገናና ስም ያተረፉት ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በአዲሱ ካቢኔ በነበሩበት ቦታ አለመቀጠላቸው ብዙዎችን እያነጋግሮ ነበር።
ነገር ግን በዛሬው ዕለት በሚኒስትር ማዕረግ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና የሕዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪና አማካሪ ሆነው ተሹመዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ትላንት የአዲሱ ካቢኔ አባሎቻቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ሹመት ማሰጠታቸው ይታወሳል።
ቀድሞ በዶ/ር ኢ/ር ስለሺ ይመራ የነበረው ሚንስቴር መሥሪያ ቤት ውስጥ የነበረው እና በአዲሱ ካቢኔ ራሱን ችሎ እንደ አዲስ የተዋቀረው የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት በሚኒስትርነት እንዲመሩ የተሾሙት ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ናቸው።
ቀሪው ከፍል የውሃ እና ኢነርጂ ሚንስትር በመባል የተሰየመውን መሥሪያ ቤት እንዲመሩ የተሾሙት ደግሞ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ናቸው።
ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ አዲስ ተሿሚ ሚንስትሮችን "እንኳን ደስ አላችሁ" ብለው ለቀጣይ አምስት ዓመታት ብሩህ የሥራ ዘመንም ተመኝተውላቸዋል።
የበጎ ሰው ሽልማትን ጨምሮ የተለያዩ የእውቅና ሽልማቶች የተሰጧቸው ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ "ግድቡ የእኔ ነው" ወይም "Its My Dam" በሚለው ንግግራቸው ይታወሳሉ።
ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ሕዳሴ ግድቡ ሲጠናቀቅ ማን ነው የሚያስተዳድረው? የሚል አንድምታ ያለው ጥያቄ ከአንድ የውጭ አገር ጋዜጠኛ በቀረበላቸው ወቅት ነበር "Its My Dam" የሚል ምላሽ የሰጡት።
ይህ አባባል በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል በግድቡ ዙሪያ ውዝግብ በተባባሰበት ወቅት በርካታ ኢትዮጵያውያን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እና በሌሎች መድረኮች ላይ አባባሉን በስፋት ጥቅም ላይ አውለውታል።
ግብፅ እና ሱዳን ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ስለ ግድቤ ቅሬታ ባሰሙባቸው ሁለት ውይይቶች ተገኝተው ምላሽ የሰጡት የቀድሞው ሚንስትር በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አግኝተውም ነበር።
"ወደድንም ጠላንም ከአንድ ወንዝ ስለምንጠጣ መተባበርን መማር አለብን" ሲሉ ለፀጥታው ምክር ቤት ያደረጉት ንግግር ሌላው የማይረሳ አባባል ነው።
ላለፉት አምስት ዓመታት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትርን በበላይነት የመሩት ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት "ላለፉት 5 ዓመታት ስመራው የነበረውን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትር ዛሬ በጸደቀው የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች አደረጃጀት መሠረት በመሾማችሁ በጣም ደስ ብሎኛል" ብለዋል።
ሁለቱ መሥሪያ ቤቶችን "ለአገራችን ማደግና መለወጥ ወሳኝ" በማለት ገልጸዋቸዋል።
"ላለፉት አምሰት ዓመታት ሚኒስትር በመሆን በቅንነት፣ በታማኝነትና በምችለው ሁሉ አገልግያለሁ" ሲሉም አክለዋል።
አያይዘውም በቀጣይ አገሪቱ በምትፈልጋቸው ዘርፍ ሁሉ ተሰማርተው ለማገለገል ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አዲሶቹ ተሿሚዎች ኢ/ር አይሻ እና ኢ/ር ሀብታሙ "በውጤታማነት እንደምትመሩ እምነት አለኝ። አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር አደርግላችኋለሁ" ሰሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትር ሳሉ ምሁራን እና ባለሙያዎች በመሥሪያ ቤቱን በተጠሪ ተቋማቱ በማካተት መሥራታቸውንም አመልከተዋል።
"ብዙ አስቸጋሪ ጊዜያትን አሳልፈናል። ግድባችንም በጥቂት ወራት ኃይል ያመነጫል። በዚህና በሌሎችም መስኮች ያደረግሁት አስተዋጽኦ በፈታኞቹ ወቅቶችና ሰዓታት አገሬን ቀና አድርጓታል ብዬ አምናለሁ" ብለዋል የቀድሞው ሚንስትር።
በያዝነው 2014 ዓ. ም የመጀመሪያዎቹ ወራት ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ 13 ተርባይኖች መካከል ሁለቱ ተርባይኖች እስከ 750 ሜጋዋት የመጀመሪያ ዙር ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ የቀድሞው ሚንስትር ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።
የቀድሞው ሚንስተር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በፌስቡክ ባስተላለፉት መልዕክት ማገባደጃ ላይ "ለነበረኝ ትልቅ ኃላፊነትና ለተደረገልኝ ትብብር አመሰግናለሁ" ብለዋል።
በተያያዘ ዜና ከዶ/ር/ኢ/ር ስለሺ በቀለ በተጨማሪ አቶ ተፈሪ ፍቅሬ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር፣ አቶ አደም ፋራህ በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ፣ ተስፋዬ ቤልጅጌ በሚኒስትር ማዕረግ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ፣ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በሚኒስትር ማዕረግ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል።
በተጨማሪም ዶ/ር ምህረት ደበበ የአፍሪካ ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት፣ አቶ ፍስሃ ይታገሱ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ እንዲሁም አቶ አብዱራህማን ሩቤ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ተሹመዋል።