ፑቲን በአገራቸው ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ከጦርነት አዋጅ ጋር አመሳሰሉ

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ወረራ ምክንያት በምዕራባውያን ሀገራት የተጣሉትን ማዕቀቦች "ጦርነት ከማወጅ ጋር ተመሳሳይ ነው" ሲሉ ገልጸዋል ።

"ነገር ግን አምላክ ይመስገን ወደዛ አልደረሰም" ሲሉም አክለዋል።

ዩክሬን ከበረራ ቀጠና ውጭ መደረግ አለባት በሚል የዩክሬን ባለስልጣናት ከፍተኛ ግፊት እያደረጉ ሲሆን ይህንንም አስመልክቶ ፕሬዚዳንት ፑቲን የበረራ ክልከላ ሙከራ በጦርነቱ ውስጥ ቀጥታ ተሳትፎ እንደሚታይ አስጠንቅቀዋል።

ከጦርነቱም ጋር ተያይዞ በሩሲያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉ የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርገውታል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን ይህንን ያሉት በሞስኮ አቅራቢያ በሚገኘው የኤሮፍሎት ማሰልጠኛ ማዕከል ውስጥ ሴት የበረራ አስተናጋጆች ቡድን ባነጋገሩበት ወቅት ነው።

አስራ አንደኛ ቀኑን ባስቆጠረው የሩስያ ወረራን ተከትሎ ምዕራባውያን ሃገራት በሩስያ የሚያደርጉትን ማዕቀብ አጠናክረው ቀጥለዋል። እስካሁን ከተጣሉ ማዕቀቦች መካከል የፕሬዚዳንት ፑቲን የውጭ ሃብት ማገድን ጨምሮ የሩስያ ባንኮችን ስዊፍት ከተሰኘው ዓለም አቀፍ የክፍያ ስርዓት ማስወጣት ይገኙበታል።

በተጨማሪም በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በሩሲያ ውስጥ ያለውን ሥራቸውን አቁመዋል ። በያዝነው ሳምነት ቅዳሜ ፣ ዛራ ፣ ፔይፓል እና ሳምሰንግ የተሰኙት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በሩሲያ ያለውን ንግዳቸውን በቅርብ ጊዜ ያቆሙ ድርጅቶች ሆነዋል።

በአገሪቱ ላይ የተጣለው ማዕቀብ የአገሪቱን መገበያያ ገንዘብ ሩብል በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሽቆለቆል ያደረገው ሲሆን የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ የወለድ ተመኖችን በእጥፍ እንዲጨምር አስገድዶታል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን በቅርቡ በሰጡት አስተያየት፣ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስረዳት ሞክረዋል። የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰቦችን በሀገሪቱ እየተደረገ ካለው "ከፍተኛ ወታደራዊነትና ናዚነት" ጥፋት ለመከላከል እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

የምዕራባውያን የመከላከያ ተንታኞች የሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻ እንደተጠበቀው እየሄደ አይደለም ለሚሉት አስተያየትም ፕሬዚዳንቱ ምላሽ ሰጥተዋል "ሠራዊታችን ሁሉንም ተግባራት ይፈጽማል። ምንም ጥርጥር የለኝም። ሁሉም ነገር በእቅድ እየሄደ ነው" ብለዋል።

በጦርነቱ ላይ የሚሳተፉት በሙያቸው ወታደሮች የሆኑ ብቻ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ምንም አይነት ተቃራኒ ዘገባዎች ቢኖሩም ዜጎች በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ውትድርና አለመግባታቸውን ገልጸዋል።

የሩሲያው መሪ በዩክሬን ሰማይ ላይ በረራ ለመከልከል የሚደረገው ጥረት ወታደራዊ ግጭቱን አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚወስደውና ተሳታፊዎቹም እንደ ጠላት ተዋጊ እንደሚወሰዱ ተናግረዋል።

"አሁን ያለው አመራር በአሁኑ ተግባራቸው ከቀጠሉ የዩክሬንን የወደፊት እድል አደጋ ላይ እንደሚጥሉ ሊገነዘቡ ይገባል" ሲሉም አክለዋል።