ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መንግሥት የእርዳታ አቅርቦቶች ወደ ትግራይ እንዲደርሱ በረራዎችን እንደሚያቀላጥፍ አስታወቀ
የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ መድኃኒት እና ምግብ ያሉ መሠረታዊ የእርዳታ አቅርቦቶችን ወደ ትግራይ ክልል ለማድረስ የሚደረጉ ዕለታዊ በረራዎችን እንዲቀላጠፉ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
መንግሥት ይህን ያለው ከሦስት ቀናት በፊት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መተላለፊያ መስመር ላይ ጦርነት በመኖሩ ወደ ትግራይ የማደርሰው የረድኤት አቅርቦት መስተጓጎል ገጥሞታል ካለ በኋላ ነው።
የመንግሥታቱ ድርጅት በአፋር ክልል አብአላ በኩል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት እንደ ምግብ እና መድኃኒት ያሉ መሠረታዊ የሰብዓዊ አቅርቦቶቹን ለመቀነስ፣ ለማራዘም እና ለመሰረዝ ተገድጃለሁ ብሎ ነበር በመግለጫው።
የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ጽ/ቤት (ኦቻ) "ከሰመራ-በአብአላ-መቀለ በሚወስደው መስመር በኩል ወደ ትግራይ የሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች አብአላ ላይ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ማክሰኞ ታኅሣሥ 05/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተቋርጦ ይገኛል" ብሎ ነበር ሐሙስ ጥር 12/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ላይ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ትግራይ የሚቀርበውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በተመለከተ እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫው ላይ፤ የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ያለውን ከፍተኛ የሕክምና መገልገያዎች አቅርቦት ፍላጎትን ይረዳል ብሏል።
ሚኒስቴሩ መንግሥት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ጥረት ቢያደርግም፤ ፍቃድ የተሰጣቸው መድኃኒቶች እና የሕክምና አቅርቦቶች ካለፈው ወር ወዲህ በህወሓት ዳግም ጥቃቶች ምክንያት ከአብአላ ማለፍ አልቻሉም ብሏል።
በዚህም ምክንያት በየብስ ከሚደረግ የእርዳታ አቅርቦት ሥራ በተጨማሪ የፌደራሉ መንግሥት መሠረታዊ ሰብዓዊ እርዳታዎችን በአየር ለማድረስ ዕለታዊ በረራዎችን እንደሚያመቻች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህን ተከትሎም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ጤና ሚኒስቴር እና ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እና ከሌሎች የተመድ ድርጅቶች ጋር በመሆን በእቃ ጫኝ አውሮፕላን በዕለታዊ በረራዎች መሠረታዊ የሆኑ መድኃኒቶችን እና አቅርቦቶችን ለማድረስ ያስተባብራል ብሏል።
የጤና ሚኒስቴርም አጋር ድጅቶች የማይኖራቸውን መድኃኒቶች እና አቅርቦቶችን ለማድረስ እየሰራ ነው ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ።
በትግራይ ክልል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በእጅጉ ተስተጓጉሎ መቆየቱን የመንግሥታቱ ድርጅትና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ሲገልጹ የቆዩ ሲሆን የህወሓት መሪዎች መንግሥት ሆን ብሎ እገዳ ጥሏል ብለው ሲከሱ፣ መንግሥት በበኩሉ እርዳታው የተስተጓጎለው የህወሓት ኃይሎች በአቅርቦት መስመሮች በኩል በሚፈጽሙት ጥቃት ሳቢያ ነው ይላል።
በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፋቶ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና የንብረት ውድመት አስከትሏል።
14 ወራትን ያስቆጠረው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ስለመቅጠፉ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ስለማፈናቀሉ በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በጦርነቱ ሳቢያ በተከሰተው ቀውስ ከ9.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሳምንታት በፊት አስታውቋል።
ጦርነቱ ያስከተለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመግታት ተዋጊ ኃይሎች ጦርነቱን በአስቸኳይ አቁመው ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ተመድን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።