ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታሊባን ከምዕራባውያን አገራት ባለሥልጣናት ጋር በኦስሎ ንግግር ጀመረ
ታሊባን ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓ ምድር ከምዕራባውያን አገራት ባለሥልጣናት ጋር ንግግር ጀመረ።
ታሊባን እና ምዕራባውያኑ ባለሥልጣናት ለሦስት ቀናት በሚዘልቅ ውይይታቸው ስለ ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ ይነጋገራሉ ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት 95 በመቶ የሚሆኑት አፍጋናውያን በቂ ምግብ የላቸውም ይላል።
በአሁኑ ወቅት በአፍጋኒስታን የሥራ አጥ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። የምግብ ዋጋ ንሯል፤ የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ዋጋ እያጣ ነው። ባንኮችም ወጭ በሚደረግ የገንዘብ መጠን ላይ ገደብ ጥለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት 55 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ለረሃብ ተጋላጭ ነው ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።
ዛሬ ሰኞ ጥር 16/2014 ታሊባን እና ምዕራባውያኑ ጥብቅ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ታሊባን በአሜሪካ ባንኮች ውስጥ እንዳይንቀሳቀስ የታገደው በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ እንዲለቀቅለት ይጠይቃል ተብሏል።
"ለአፍጋን ሕዝብ ገንዘብ እንዲለቁ እየጠየቅናቸው ነው። በፖለቲካ ልዩነት የአፍጋኒስታን ዜጎች ሊጎዱ አይገባም" ሲሉ የታሊባን ተወካዩ ሻፊኡላህ አዛም ለአሶሺዬትድ ፕሬስ ተናግረዋል።
ተወካዩ በአፋጋኒስታን ተጋርጧል በተባለው ረሃብ እና በአገሪቱ ባለው ከባድ ቅዝቃዜ ምክንያት ዓለም አቀፉ ማሕብረሰብ አፍጋኒስታንን መርዳት እንጂ መቅጣት የለበትም በማለት ጨምረው ተናግረዋል።
ታሊባን እና ምዕራባውያኑ በሚያደርጉት ውይይት ላይ የምዕራባውያኑ ተወካዮች ቡድኑ የበለጠ አካታች እንዲሆን እና የሰብዓዊ መብት ጥበቃዎች ላይም ትኩረት ያደርጋሉ።
ታሊባን አፍጋኒስታንን መልሶ ከተቆጣጠረ ወዲህ ሴት ሠራተኞች በቤት እንዲቆዩ ማዘዙ ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪም ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች ለወንድ ተማሪዎች እና ለወንድ መምህራን ብቻ ከፍት ሆነዋል።
ይህን የታሊባን ሥርዓት የተቃወሙ በርካታ ሴቶች በቡድኑ ዒላማ ተደርገዋል። አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ አድራሻቸው የጠፉ ሴቶች አሉ። ታሊባን በበኩሉ ከሴቶቹ መጥፋት ጋር የሚያገናኘኝ የለም ይላል።
ከመብት ተከራካሪ ሴቶች በተጨማሪ ጋዜጠኞችም በታሊባን ዒላማ ሲደረጉ ቆይተዋል።
እስካሁን ድረስ የትኛውም አገር ለአዲሱ የታሊባን መንግሥት እውቅና አልሰጠም።
የኖርዌይ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አኒከን ሁኢትፌልደት ምዕራባውያን ከታሊባን ጋር የሚያደርጉት ውይይት ቡድኑ ለመሠረትው መንግሥት እውቅና መስጠት አይደለም ብለዋል።
የታሊባን እና ምዕራባውያን አገራት ባለሥልጣናት ለውይይት መቀመጥ በአፍጋኒስታን የተከፋፈለ ስሜትን ፈጥሯል።
አንዳንዶች ምዕራባውያኑ ከቡድኑ ተወካዮች ጋር መነጋገራቸው መልካም ነው ሱሉ ገሚሱ ደግሞ ታሊባን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸመ በአውሮፓ ከተሞች ላይ ለውይይት መጋበዙ ትክክል አይደለም ይላሉ።
የውይይቱን መካሄድ የሚቃወሙ ሰልፎች በአውሮፓ ከተሞች ተካሂደዋል።