ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ወታደሮች በዩክሬን ለመሰማራት በተጠንቀቅ ላይ ናቸው
ወደ 8 ሺህ 500 የሚሆኑ ለውጊያ ዝግጁ የሆኑ የአሜሪካ ወታደሮች ውጥረት እየጨመረባት ባለው ዩክሬን በአጭር ጊዜ ለማሰማራት በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን ፔንታጎን አስታወቀ።
ሩሲያ ምንም እንኳን 100 ሺህ ያህል ወታደሮችን ወደ ድንበሩ አቅራቢያ ብታስጠጋም በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ጥቃት ልትወስድ አቅዳለች መበሏን አትቀበለውም።
ሩሲያ እየተዘጋጀችበት ነው ባሉት ወረራም ላይ ፕሬዚዳንት ባይደን ከምዕራቡ ዓለም ኃይሎች አጋሮቻቸው ጋር ስትራቴጂን ለመንደፍ በያዝነው ሳምንት ሰኞ በቪዲዮ ውይይት አድርገዋል።
ፔንታጎን ወታደሮቹ በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን ቢያስታውቅም የማሰማራቱን ጉዳይ እስካሁን ምንም አይነት ውሳኔ አልተላለፈም።
ወታደሮቹ የሚሰማሩት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በፈጣን ምላሸ ሰጪ ኃይል እርምጃ የሚወስድ ከሆነ ወይም በሩሲያ ኃይል ዙሪያ ሌሎች ሁኔታዎች ከተፈጠሩ እንደሆነም የፔንታጎን የፕሬስ ሴክሬታሪ ጆን ኪርቢ ተናግረዋል።
በዩክሬን ውስጥ የማሰማራት እቅድ የለም ሲሉ አክለዋል።
ዴንማርክ፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ እና ኔዘርላንድስን የመሳሰሉ የኔቶ አባላት ከወዲሁ በአካባቢው ያለውን መከላከያ ለማጠናከር የጦር ጄቶች እና የጦር መርከቦች ወደ ምስራቅ አውሮፓ ለመላክ እያሰቡ ነው።
በሳምንቱ መጨረሻም በግንባር ላሉ ተዋጊዎች " ጥይቶችን ጨምሮ 90 ቶን የአሜሪካ የጦር መሳሪያ እርዳታ ወደ ዩክሬን ገብቷል።
በሰኞው የፕሬዚዳንት ባይደን የቪዲዮ ጥሪም የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ፣ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፣ የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ፣ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪዮ ድራጊ ፣ የፖላንድ ፕሬዝዳንት አንድርዜጅ ዱዳ እና የኔቶ ኃላፊ ጄንስ ስቶልተንበርግም ተሳታፊ ነበሩ።
በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረት ኃላፊዎች ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን እና ቻርለስ ሚሼል እንዲሁ በውይይቱ ላይ ተገኝተው እንደነበር ተገልጿል።
"በጣም ጥሩ ስብሰባ ነበር - ከሁሉም የአውሮፓ መሪዎች ጋር አጠቃላይ አንድነትም ነበረን።" ብለዋል ባይደን