ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የካሜሩን ጨዋታን ለማየት በተፈጠረ ግርግር ሳቢያ ስምንት ሰዎች ሞቱ
የአፍሪካ ዋንጫን እያዘጋጀች ባለችው ካሜሩን ከሚገኝ አንድ ስታድየም መግቢያ ላይ በተከሰተ አደጋ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው ተዘገበ።
ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንደሚያሳዩት እግር ኳስ ለመታደም የመጡ ሰዎች ዋና ከተማዋ ያውንዴ ወደሚገኘው ፖል ቢያ ስታድየም ለመግባት ትግል ላይ ነበሩ።
የካሜሩን ማዕከላዊ ግዛት አስተዳዳሪ ናስሪ ፖል ቢያ አደጋው ጉዳት ሳያስከትል አልቀረም ማለታቸውን ኤፒ አስነብቧል።
ሌሎች ዘገባዎች ደግሞ ሕፃናት በግርግሩ ሳቢያ ራሳቸውን ስተው እንደነበር ተናግረዋል።
ስታድየሙ 60 ሺህ ሰው የመያዝ አቅም ቢኖረውም በኮቪድ ምክንያት ከ80 በመቶ በላይ ሰው እንዳይገባ ተደርጎ ነበር።
ጨዋታውን የሚያሳልጡ ሰዎች ቢያንስ 50 ሺህ ሰዎች ጨዋታውን ለመታደም እንደተገኙ ገልጠዋል።
ብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲአርቲቪ በአደጋው ሳቢያ "ቢያንስ ግማሽ ደርዘን ሰዎች ሞተዋል፤ በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል" ብሏል።
የቢቢሲ አፍሪካው ኒክ ካቭል ጨዋታውን ለመታደም በስታድየም ቢገኝም የአደጋው ዜና በማሕበራዊ ድር አምባ እስኪሰራጭ ድረስ ስታድየም ውስጥ የነበርን ሰዎች አልሰማንም ይላል።
በርካታ ጫማዎችና ስብርባሪዎች በስታድየም መግቢያ በር ዙሪያ ተበታትነው መታየታቸውን ኒክ ይናገራል።
ነርስ ኦሊንጋ ፕሩደንስ ለኤፒ እንደተናገረችው አንዳንድ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች "ለሕይወታቸው እየታገሉ ነው።"
የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ካፍ ባወጣው መግለጫ አደጋውንና የአደጋውን ምክንያት እያጣራ መሆኑን ገልጧል።
በትላንትናው ጨዋታ ካሜሩን ከኮሞሮስ ወደ ሩብ ፍፃሜ ለማለፍ ተፋልመዋል።
በኮቪድ ምክንያት በርካታ ተጫዋቾቿን ያጣችው ኮሞሮስ ሶስቱም ግብ ጠባቂዎች መሰለፍ ባለመቻላቸው ምክንያት ተከላካዩ ጓንቱን አጥልቆ ገብቷል።
ጨዋታው በተጀመረ በ6ኛው ደቂቃ የመሃል ዳኛው ባምላክ ተሰማ ጥፋት ፈፅሟል ያሉትን የኮሞሮስ ተጫዋች በቀይ አስወጥተዋል።
ፍልሚያው በማይበገሩት አንበሶች 2-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን አዘጋጇ ካሜሩን በቀጣይ ከጋምቢያ ትገጥማለች።