ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አየርላንድ ውስጥ የሟችን ጡረታ ለመውሰድ አስክሬኑን ፖስታ ቤት የወሰዱ ግለሰቦች እየተፈለጉ ነው
አየርላንድ ውስት የአንድን ግለሰብ የጡረታ ገንዘብን ለመውሰድ ሲሉ አስክሬኑን ወደ ፖስታ ቤት ይዘው የሄዱ ሰዎችን በተመለከተ ፖሊስ ምርመራ መካሄድ መጀመሩ ተዘገበ።
አይሪሽ ታይምስ እንደዘገበው ሁለቱ ሰዎች የሟችን አስክሬን በሕይወት ያለ አስመስለው ካውንቲ ካርሎ በተሰኘ ሕንጻ ውስጥ ወደሚገኝ ፖስታ ቤት ወስደውታል።
የፖስታ ቤቱ ሠራተኞች ግን ስለሁኔታው ስለሁኔታው በጥያቄ ሲያጣድፏቸው አስክሬኑን እዚያው ትተተው ሸሽተዋል።
የአየርላንድ ፖሊስ ግልጽ ያልሆነውን በእድሜ የገፋውን ግለሰብ አሟሟት እየመረመረ እንደሆነ ገልጿል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ አርብ ዕለት ጠዋት በፖስታ ቤቱ ውስጥ ስለተከሰተው ነገር ዝርዝር ጉዳዮች ላይ መረጃ እንደማይሰጥ በመግለጽ አጭር መግለጫ አውጥቷል።
የአየርላንድ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ "የግዛቱ ቴክኒካዊ ቢሮ እና የፓቶሎጂስት እገዛ ተጠይቋል። አስክሬኑ ከተመረመረ በኋላ ምርመራው በምን አቅጣጫ እንደሚሄድ እንወስናለን" ብሏል።
ሁለቱ ግለሰቦች አስክሬኑን ፖስታ ቤት የወሰዱት "ደኅና እንደሆነ አስመስለው" እንደነበር ተገልጿል።
አንድ የፖስታ ቤቱ ሠራተኛ ስለ ግለሰቡ ደኅንነት ሲጠይቃቸው ግን አስክሬኑን ፖስታ ቤቱ ውስጥ ጥለው ሸሽተዋል።
የፖስታ ቤቱ ሠራተኞች ሰዎቹ ትተውት የሄዱትን ግለሰብ ሲፈትሹ በዕድሜ የገፋ ሰው አስከሬን መሆኑን ለማወቅ ችለዋል።
አስክሬኑ ወደ ፖስታ ቤት ከመወሰዱ በፊት አንድ ግለሰብ ወደ ፖስታ ቤቱ ደውሎ፤ "የአንድ ሰውን ጡረታ መቀበል እፈልጋለሁ" ብሎ ነበር።
ነገር ግን የጡረታው ባለቤት ከሌለ ጡረታው እንደማይሰጠው የፖስታ ቤቱ ሠራተኞች ምላሽ ሰጥተውታል።
ከዚህ የስልክ ንግግር በኋላ ነው ሁለቱ ሰዎች የ60 ዓመቱን ግለሰብ አስክሬን ወደ ፖስታ ቤት ይዘው የሄዱት።
ፖስታ ቤቱ ወንጀል የተፈጸመበት አካባቢ ተብሎ የተዘጋ ሲሆን፤ ፖሊስም ምርመራው እኣካሄደ ነው።
ሟቹ ወደ ፖስታ ቤት የተወሰደው ከሞተ በኋላ ስለመሆኑ ወይም ፖስታ ቤት ከደረሰ በኋላ ሕይወቱ ስለማለፉ እስካሁን አልታወቀም።