ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"የተጠየቅኩባቸው ጉዳዮች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር የሚገናኙ አልነበሩም" እያስፔድ ተስፋዬ
ማኅበራዊ አንቂና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ሲሰራ የቆው ከኢያስፔድ ተስፋዬ ከ43 ቀናት የእስር ቆይታ በኋላ ከቀናት በፊት ተለቋል።
ኢያስፔድ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት አስር ዓመታት ያህል በተለያዩ ወቅቶች የቅርቡን ጨምሮ ለዘጠኝ ጊዜያት ያህል ታስሯል። ነገር ግን ከአንድ ወር በላይ ሲታሰር የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።
ከአንድ ባልደረባው ጋር በቅርብ በመሰረቱት 'ኡቡንቱ' በተሰኘ ዩቲዩብ ቴሌቪዥን ላይ ሲሰራ ከነበረው ኢያስፔድ ከአስር ከወጣ ከቀናት በኋላ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጓል።
ቢቢሲ፡ በታሰርክበት ወቅት ታመህ እንደነበር ከቤሰተቦችህ እና ከወዳጆችህ ስንሰማ ነበር። ህክምና እንዳላገኘህም ጭምር። ምን ነበር ያጋጠመህ?
እያስፔድ፡ የኢትዮጵያ እስር ቤቶች እንደሚታወቀው በጠባብ ቦታ ውስጥ በርካታ ሰው ይታሰራል። ከንጽህና ጉድለት የሚመጡ በሽታዎች እና በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታዎች ያሉ ናቸው። የተለየ ነገር ከመታሰሬ ከጥቂት ቀናት በፊት የጥርስ ህክምና ጀምሬ ነበር። ይህ እንደሚታወቀው ሂደት አለው።
የመጀመሪያ ቀን ህክምናውን ጀምሬ እሱን አቋርጬ ነው የታሰርኩት። በእሱ በጣም ተቸግሬ ነበር። ወደተሻለ ህክምና ለመሄድ ብጠይቅም ፈቃደኛ አልነበሩም። በ43 ቀን ውስጥ ከ7 ኪሎ በላይ ቀንሼ ነው የወጣሁት።
ቢቢሲ፡ በታሰርክበት ቀን ስለ ነበሩ ነገሮች የተወሰኑ ነገሮች ሰምተናል። በአጭሩ ግን እንዴት እንደነበር ንገረን?
እያስፔድ፡ ቤት ውስጥ ነበርኩ በአጋጣሚ። በዚያ ሰሞን በርካቶች ይታሰር እያሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ዘመቻ ያደርጉ ነበር። እናም ያን ያህል እንቅስቃሴ አላደርግም ነበር። ስለዚህ በጣም በርካታ ፖሊስ፣ የፌደራል ፖሊስ እንዲሁም በርካታ መኪኖች ነበሩ። በጣም ትልቅ ወንጀለኛ የሚያዝ ነበር የሚመስለው። ያው አብዛኛው ሰው በተያዘበት መልኩ የቤትና የቢሮ ብርበራዎች ተደርገው ነበር። ብዙ የተለየ አልነበረም።
ቢቢሲ፡ በጠቀስከው የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ምክንያት ነው ብለህ ታምናለህ? ወይም በአጠቃላይ ከታሰርክ በኋላ ለምን እንደታሰርክ የተሰጠህ ምክንያት አለ?
እያስፔድ፡ በአጠቃላይ ሁለት ቀን ለምርመራ ተጠርቼ ነበር። አንደኛው የገባሁ ቀን ሌላ ቀን ደሞ ከታሰርኩ ከአንድ ወር በኋላ። ሁለቱም ቀን የተነገሩኝ ነገሮች ይለያያል። የመጀመሪያ ቀን አንድ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚታወቅ አካውንት አለ። መረጃ ደርሶናል እሱ አንተ ነህ ወይ? የሚል ነው። ለማስረዳት ሞክሬ የተቀበሉኝ ይመስለኛል።
ከ30 ቀን በኋላ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሰራው እና ለክስ መነሻ የሚሆን የሚዲያ ሞኒተሪንግ (ክትትል) ሰነድ ልኮላቸው ነበር። በጣም የደነቀኝ ነገር ከወቅታዊ ነገሮች ጋር አይገናኝም። ወደ ኋላ የዛሬ ሦስት ዓመት ተመልሶ በአዲስ ቲቪ አንድ የክርክር መድረክ ላይ የተናገርኳቸውን ነገሮች የሚዘረዝር ሰነድ ነው። እኔ እንደጠረጠርኩት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ብዙም የሚገናኝ ነገር የለውም።
ቃል የሰጠሁበት የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በጻፈው ክስ ላይ ነው። ለምሳሌ የዛሬ ሦስት ዓመት "የሶማሌ ሕዝብ ባሕል፣ ማንነት እና ወዘተ በኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ አልተገለጸም ብሎ በአዲስ ቲቪ ላይ በመናገር አንድን ሕዝብ በሌላው ላይ ለማነሳሳት ሞክሯል" የሚል ይገኝበታል።
የዛሬ ሁለት ዓመት ቢቢሲ ላይ ይመስለኛል ቀርቦ አንድን ሕዝብ ሊያነሳሳ ሞክሯል የሚሉ ወደ 10 ገጽ የሚሆኑ፣ ወቅታዊ ያልሆኑ እና ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ ስናገራቸው የቆዩ ነገሮች እየተለቀሙ ክስ በሚመስል መልኩ ነው የመጡት።
በእርግጥ በቅርብ የተናገርኳቸው ነገሮችም ተጨምረዋል። አጠቃላይ ይዘቱ ግን እኔ እንደሚታወቀው አሁን ያለው የፌደራል ሥርዓት ደጋፊ ነኝ። ያንን በተመለከተ የተናገርኳቸው ነገሮች ናቸው ሕዝብን ከሕዝብ እንደማጋጨት የታዩት።
ቢቢሲ፡ ስትፈታስ በምን ምክንያት ነው እንድትለቀቅ የተወሰነው?
እያስፔድ፡ ፖሊስ የመታወቂያ ዋስ የሚለው ነገር አለ፤ በእሱ ነው የወጣሁት። እንደሚመስለኝ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንም ይሁን ከተለያዩ አካላት የደረሳቸው ነገሮች ክስ ለመመስረት በቂ አለመሆኑን ተረድተው ነው ብዬ አስባለሁ። ሚዛን የሚያነሳ ነገር ስላልነበረ ተለቅቄያለሁ ብዬ አምናለሁ።
ቢቢሲ፡ ተባባሪ መስራች የሆንክበት ኡቡንቱ ቲቪ ንብረቶቹ ተመልሰዋል ወይ? በቅርቡ ወደ ሥራ የመመለስ እቅድስ አላችሁ?
እያስፔድ፡ ሚዲያችን ተበርብሮ ነበር። እቃዎቹም ተወስደዋል። እንደሚታወቀው የሚዲያ እቃዎች ውድ ናቸው። በርካታ ካሜራዎች እና ቁሳቁሶች ተወስደውብናል። ሲወሰዱ በቃለ ጉባኤ ምስክር ባለበት ተፈርሞ ነው የተወሰዱት።
እነዚህ እቃዎች የሚመለሱት ዐቃቤ ሕግ እቃዎቹ ከዚህ በኋላ አያስፈልጉም ለባለቤቱ ይመለስ ካለ በኋላ በመሆኑ እንደተፈታሁ እቃዎቹን ለማግኘት አልቻልኩም። ፖሊስ ለመመለስ ፈቃደኛ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህ የሥነ ሥርዓት ጉዳይ ስለሆነ እሱ እንዳለቀ ይመለሳል ብዬ አስባለሁ።
ነገር ግን እቃዎቹ ተመለሱም አልተመለሱም ሚዲያችን በሚቀጥሉት ሁለት እና ሦስት ቀናት ውስጥ ይመለሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ተመልሰን ሥራችንን ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ ነን።
ቢቢሲ፡ ታስረህበት በነበረው ጣቢያ ሌሎች ጋዜጠኞች ነበሩ? እነማን ናቸው? ሁኔታውስ ምን ይመስላል?
እያስፔድ፡ የተለያዩ ቦታዎች ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ከወጣሁ በኋላም ውስጥም ሆኜ ሰምቻለሁ። እኔ የታሰርኩበት ቦታ የኤፒ ጋዜጠኛ የነበረው አሚር አማን እና የካሜራ ባለሞያው ቶማስ እንግዳ ይገኙ ነበር። እስካሁን በእስር ላይ ነው ያሉት።
እንደሚታወቀው የጋዜጠኝነት ሥራ ብዙ ውጣ ውረድ ያለው እና ብዙ ሪስክ (አደጋ) ተወስዶ የሚሰራ ሥራ ነው። እነሱም ያንን የጋዜጠኝነት ሥራ ነው ሲሰሩ የቆዩት። ምን አልባት መንግሥት የማይወዳቸውን አካላት አናግረው ሊሆን ይችላል።
ይህ ግን በጋዜጠኝነት ሥራ እንደ ወንጀል ይሚታይ ነው ብዬ አላስብም። ወንጀል ነው ከተባለም ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት ሊኖራቸው ይገባል። እኔ እስከምወጣ ድረስ ፍርድ ቤት አልቀረቡም።
ስለዚህ መንግሥት የቀሩትን ጋዜጠኞች በሙሉ መፍታት ይገባዋል። ለእኛ ደረሰው እድል ለእነሱም እንዲደርስ አደራ እላለሁ።
ቢቢሲ፡ በእስር ላይ የነበሩ ፖለቲከኞች እንዲፈቱ ዘመቻዎችን ስታስተባብር እንደነበር ይታወቃል። በታሰርክበት ወቅት ነው እነዚህ ሰዎች የተፈቱት። እንዴት ነበር ዜናውን የሰማኸው ምን ነበር ስሜቱ?
እያስፔድ፡ እርግጥ ነው ላለፈው አንድ ዓመት በላይ ዘመቻዎችን እና እንቅስቃሴዎችን ስናደርግ ቆይተናል። መንግሥት በመጨረሻም ወደዚህ አቋም መምጣቱ በራሱ የሚያስደስት ነው።
በተፈቱ በማግስቱ ነው ዜናውን የሰማነው። አብዛኛው ሰው ራሱ እንደተፈታ ነው የቆጠረው። እኔ ራሴ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። ራሴ የተፈታሁ ያህል ነው ደስ ያለኝ። አንዳንዶቹ ከፖለቲካ አቋምም ባለፈ ወዳጆቼ ስለሆኑ ደስ ብሎኛል።
በአጠቃላይ ግን ሁለት እንድምታዎችን ማንሳት አለብኝ። አንደኛው ለረጅም ጊዜ ስንለው እንደነበር እስረኞች ተፈተው ሁሉም ነገር ወደ ጠረጴዛ መምጣት አለበት የሚለውን፤ የፖለቲካ ልዩነቶች በሰላም በጠረጴዛ ዙሪያ ይፈቱ የሚለው እኔ በግሌም በሚዲያችንም ስንለው ቆየነው ነው። መንግሥት ይህንን እርምጃ መውሰድ መጀመሩ የሚበረታታ ተግባር ነው።
ነገር ግን አሁንም በርካታ እስረኞች ይቀራሉ። እኔ እንኳን ታስሬ በነበርኩበት ቦታ በርካታ ጋዜጠኞችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች አሉ። በተለያዩ እስር ቤት የተለያዩ የፓርቲ አመራሮች አሉ። እርምጃው የተቆራራጠ ባይሆን ጥሩ ነው። ያ ካልሆነ የተወሰነ የፖለቲካ ነጥብ ለማግኘት የሚደረግ እና ተመልሰን ወደነበርበት አዘቅት ውስጥ እንዳንገባ እላለሁ። ነገሩ ካፊያ ሳይሆን ለሁሉም መዝነብ አለበት።
ከእስር ስወጣ በርካታ ነገር ተቀይሮ ነው የጠበቀኝ። አንዱ የአገራዊ ምክክር ጉዳይ ነው። ይህ መልካም ነገር ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ነገር ሞክረናል። ለመሞከር ያህል ብቻ የምናደርገውከሆነ ማግኘት ያለብንን ነገር እንዳናጣ እሰጋለሁ።
ለምሳሌ ምርጫ ተደርጓል። ለማድረግ ያህል ማድረግ እና በትክክለኛ መንገድ ማድረግ ይለያያል። እድሉን እንዳናባክነው እፈራለሁ። ብሔራዊ መግባባበትን ለመፍጠር የሚደረግ ውይይት ገና ያልተሞከረ ነገር ነው። ከተሞከረ አይቀር በደንብ ተጠንቶ እና ታስቦበት ሁሉንም ወገን ያሳተፈ ካልሆነ የአገራችንን እድል እያስመለጥን ነው ብዬ አስባለሁ።
ከመነሻው ጀምሮ የኮሚሽነሮችን ምርጫ፣ ተሳታፊ መምረጥ ብሎም መርሃ ግብሩን ማዘጋጀት ላይ የተለያዩ አመለካከቶችን ያሳተፈ መሆን አለበት። ሰርቶ እና ጨርሶ "ኑ እና እኔ ያቦካሁትን ጋግሩ" መሆን የለበትም።
ቢቢሲ፡የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንደሚከታተል ሰው ጦርነቱን በተመለከተም ያሉ ለውጦችን ጨምሮ አሁን ያሉ የፖለቲካ እውነታዎች በአጠቃላይ በምኅዳሩ ላይ ምን ውጤት ይዘው የሚመጡ ይመስልሃል?
እያስፔድ፡ በእስር ላይ ስለነበርኩ በጉዳዩ ላይ ያልበሰለ እና የማይመጥን ትንታኔ እንዳልሰጥ ስለምሰጋ አንድ ነገር ብቻ ልበል።
ጦርነቱን በተመለከተ መስከረም አንድ ላይ ምን ሊመጣ ይችላል የሚሉ የቢሆን መላምቶችን አስቀምጠን ነበር። አንዱ ካስቀመጥናቸው ግምቶች ውስጥ በጦርነቱ ውስጥ በቆዩ ቁጥር በሁለቱም አካላት ዘንድ ዝለት ይመጣል ብለን ነበር። ጦርነት ኢኮኖሚንም ሆነ የሰው ህይወትን የሚበላ አድካሚ ነገር ነው ብለን ነበር።
ሁለቱም ወገኖች አሁን ወደ ዝለት ሲመጡ ለድርድር ይቀመጣሉ የሚል ትንታኔ ሰጥተን ነበር። አሁን ወደዚያ ዝለት እየሄዱ ይመስለኛል። ሁለቱም አካላት ይህንን እድል እንደ ጊዜ መግዣ እና ትንፋሽ መሰብሰቢያ እንደማይወሰዱት፣ ብሎም ባግባቡ እንደሚጠቀሙበት ተስፋ አደርጋለሁ።
በመጣው ነገር ደስተኛ ያልሆኑ አካላት እንዳሉ ይሰማኛል። ከደረሰው ውድመት ብሎም ወደፊት ከሚደርሰው ውድመት ይልቅ አሁን የተወሰዱ እርምጃዎች ይሻላሉ ሊበረታቱም ይገባል ብዬ ነው የማስበው። በተጀመረው ቅድመ ውይይት ላይ ትኩረት ቢደረግ መልካም ይመሰለኛል።