የ88 ዓመቱ ተመራቂ፡ 'ትምህርት በ20 ዓመት ወጣት ያደርጋል'

የ88 ዓመቷ አዛውንት ዶ/ር ሩte ዊልሰን (ከመሐል) ከባለቤታቸው ዴቪድ ዊልሰን (ግራ) እና ከዩኒቨርስቲው ቻንስለር ዶ/ር ቤሪ ካትቸሎቭ

የፎቶው ባለመብት, University of Sydney

የምስሉ መግለጫ, የ88 ዓመቷ አዛውንት ዶ/ር ሩte ዊልሰን (ከመሐል) ከባለቤታቸው ዴቪድ ዊልሰን (ግራ) እና ከዩኒቨርስቲው ቻንስለር ዶ/ር ቤሪ ካትቸሎቭ

በምናባችሁ ስለ ዩኒቨርሲቲ አልያም ስለ አንድ የትምህርት ተቋም ስታስቡ ቶሎ ወደ ጭንቅላታችሁ የሚመጣው በሃያዎቹ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ወደ መማሪያ ክፍል ለመግባት ሲጣደፉ አልያም ሰብሰብ ብለው ሲጨዋወቱ ነው።

ትንሽ እድሜያቸው ገፋ ያሉ ሰዎች ደግሞ ያለምንም ጥርጥር መምህራንና የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚደግፉ ሠራተኞች እንደሆኑ ነው የሚታሰበው።

ነገር ግን የሰው ልጆች በሕይወት የሚቆዩበት ጊዜ በረዘመ ቁጥር እድሜያቸው የገፋ ሰዎችም ጭምር ያሏቸውን ቀሪ ዓመታት በትምህርት ለማሳለፍ እየወሰኑ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ጥር 16ን ዓለም አቀፍ የትምህርት ቀን አድርጎ የሚያከብር ሲሆን ቢቢሲም ይህንን በማስመልከት በኢንዶኔዢያ፣ በካናዳ፣ በብራዚል እና በአውስትራሊያ የሚኖሩ እድሜያቸው የገፋ ነገር ግን በቆራጥነት ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ሰዎችን አነጋግሯል።

ብራዚል፡ "የተሻለ ማበረሰብ ለመፍጠር አሁንም አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን"

የ70 ዓመቷ ተማሪ አንቶኒያ ላንጋርፍ

የፎቶው ባለመብት, Antonia Landgraf

የምስሉ መግለጫ, የ70 ዓመቷ ተማሪ አንቶኒያ ላንጋርፍ

አንቶኒያ ላንጋርፍ የ70 ዓመት ተማሪ ናቸው። በማዕከላዊ ብራዚል በምትገኝ ኖቫ ዣቫንቲና የሚኖሩት እኘህ ጡረተኛ ሴት ማቶ ግሮሶ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪ ናቸው።

"ከ10 ዓመታት በፊት ከብራዚል ብሔራዊ ባንክ በጡረታ ተገልያለሁ። ነገር ግን ዝም ብዬ ቤት ውስጥ መቀመጥ አልቻልኩም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ባለቤቴ ከብቶችን የሚያረባ ሲሆን እኔ ደግሞ እሱን መርዳት እፈልጋለሁ። ነገር ግን አዳዲስ ነገሮችን መማር ደግሞ ጭንቅላቴን ሰላም ይሰጠዋል። ስለዚህ መጀመሪያ ያጠናሁት ጂኦግራፊ እና አካውንቲንግ ነው።"

ይህ የሆነው ታዲያ የዛሬ 10 ዓመት ነው። አሁን ላይ ደግሞ አግሮኖሚክስ በማጥናት ላይ ይገኛሉ የ70 ዓመቷ አንቶኒያ ላንጋርፍ።

አንቶኒያ መጀመሪያ ላይ ለጓደኞቻቸው ወደ ትምህርት ቤት መመለስ እንደሚፈልጉ ሲነግሯቸው ሁሉም የአእምሮ ጤናቸውን ተጠራጥረው ነበር።

"አንዳንዶቹ ጊዜን ማባከን አድርገው ነው የቆጠሩት። ነገር ግን የእኔ ትውልዶች አሁንም የተሻለ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የድርሻቸውን መወጣት ይችላሉ፤ አለባቸውም ብዬ አምናለው።"

"በተጨማሪም ጭንቅላታችን ሥራ እንዳይፈታ ማድረግ ተገቢ ነው። አዲስ ነገር ለመማር መቼም ቢሆን ረፍዶ አያውቅም።"

ነገር ግን መማሪያ ክፍል ውስጥ በእድሜ ከማይመሳሰሉ ወጣቶች ጋር መማር በጣም ከባድ እና አንዳንዴም ግራ የሚያጋባ ሁኔታ እንደነበር አንቶኒያ ያስታውሳሉ።

"ከአስተማሪዎቼንም ጭምር በእድሜ በልጣቸዋለሁ። በተጨማሪ ደግሞ ምንም የማይገቡኝ ቴክኖሎጂዎች አሉ። ወረርሽኙ ዓለማችንን ሲያጠቃ በበይነ መረብ አማካይነት የሚሰጠውን ትምህርት መከታተል ከብዶኝ ነበር።"

ነገር ግን አንቶኒያ ከሁሉም ነገር ጋር ተላምደው አሁን ላይ እንደውም ለምን ይሄን አንሰራም፤ ለምን ይሄን አንሞክርም የሚሉ ፈጣሪ ጭንቅላት ያላቸው ተማሪ ሆነዋል።

አውስትራሊያ፡ "ትምሀርት ወጣት ያደርጋል"

የ88 ዓመት የእድሜ ባለጸጋዋ ሩት ዊልሰን

የፎቶው ባለመብት, Dr Ruth Wilson

የምስሉ መግለጫ, የ88 ዓመት የእድሜ ባለጸጋዋ ሩት ዊልሰን

ሩት ዊልሰን የ88 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ሲሆኑ ታዋቂዋ የእንግሊዝ ፀሐፊ ጄን ኦስተን መጽሐፎች ላይ ምርምር በማድረግ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በሲድኒ ዩኒቨርሲቲ አጠናቀዋል።

እሳቸው እንደሚሉት ትምህርት በጣም አስገራሚ ልምድ ሲሆን ፍሬውም በጣም አስደሳች ነው።

"ትምህርት ወጣት ያደርጋል" ይላሉ ዶክተር ሩት።

"በጣም ብዙ የሆኑ አዳዲስ ነገሮችን ለመማር ይረዳል። በተጨማሪ ደግሞ በእኔ እደሜ የነበሩ ነገሮችንና አስተሳሰቦችን ከአሁኑ ዘመን ጋር ለማገናኘትና በደንብ ለመረዳት ይጠቅማል። እኔ እንደውም በዚህ ትምህረት ብቻ ወደኋላ 20 ዓመት የተመለስኩ ነው የሚመስለኝ"

የቀድሞዋ የእንግሊዝኛ መምህር ህጻናት ከአዲስ ሰዎች ጋር ሲቀላቀሉ እንዴት አድርገው እንደሚላመዱና አዳዲስ ነገሮችን በቶሎ እንደሚቀስሙ አስተውለው ነበር።

ታዲያ ይህ ምልከታቸው ነው ለምን እኔስ ወደ ትምህርት ቤት ገብቼ አዳዲስ ነገሮችን የማልማረው፤ ለምንስ አዳዲስ ሰዎችን አልተዋወቅም የሚል ሀሳብ የመጣላቸው።

የአራት ልጆች እናት፣ የአምስት ልጆች አያት እንዲሁም የስምንት ልጆች ቅድመ አያት የሆኑት ሩት ትምህርት ቤት ስገባ የሚሰማኝን ደስታ የትም አላገኘውም ይላሉ።

"ልጆቼ በተለይ በጣም ያበረታቱኝ ነበር። እኔ ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ ማሰቤን በጣም በጥሩ ጎኑ ነበር የተመለከቱት። አንደኛዋ ሴት ልጄ የዶክትሬት ዲግሪ ያላት ሲሆን በዩኒቨርሲቲተ ውስጥ ያለው አካሄድና አሰራር በደንብ እንድረዳ አግዛኛለች።"

"አንደኛዋ የልጅ ልጄም ብትሆን እንዲሁ ፒኤችዲ ያላት ሲሆን እሷ ደግሞ በምርምር ሥራዎቼ ላይ በጣም ረድታኛለች።"

ሩት ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረቁት በአውሮፓውያኑ 1979 ሲሆን አሁን ላይ ያለው የትምሀርት ሥርዓት በእጅጉ እንደሚለይና እንደሚያስገርማቸው ይናገራሉ።

ካናዳ፡ "የህይወት ታሪኮች አሁንም እየተጻፉ ነው"

የ70 ዓመት የእድሜ ባለጸጋዋ ሉዊስ ካሜኒትዝ

የፎቶው ባለመብት, York University

የምስሉ መግለጫ, የ70 ዓመት የእድሜ ባለጸጋዋ ሉዊስ ካሜኒትዝ

ሉዊስ ካሜኒትዝ የ70 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ናቸው። ሁሌም ቢሆን ለምን እድሜያቸው የገፉ ሰዎች ወደ ትምህርት ቤት ይገባሉ ብለው ይጠይቁ ነበር። በመጨረሻ ግን ለምን እራሴው ሄጄ አልሞክረውም ብለው ተነሱ።

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ሉዊስ ካናዳ ከሚገኘው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ በአዋቂዎች ትምህርት ላይ ምርምር በማድረግ ዶክትሬታቸውን ሰርተዋል።

በዚህ የምረምር ሥራቸው ሉዊስ እድሜያቸው ከ50 እስከ 60 የሆኑ ሰባት ሴቶች ለምን ወደ ትምሀርት ቤት እንደተመለሱ አጥንተዋል። በመጨረሻም በእድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች ካናዳ ውስጥ ወደ ትምህርት የሚመለሱት ዩኒቨርሲቲዎች አዋቂዎችን የሚጠይቁት ክፍያ አነስተኛ መሆኑን ተከትሎ እንደሆነ ደርሰውበታል።

ነገር ግን ከዚህ በተጨማሪ ሌላ ትልቅ ምክንያት አለ ይላሉ።

"ከቤተሰቤ ዩኒቨርሲቲ የገባሁት እኔ ብቻ ነኝ። የትምህርቱን ዓለም እንዴት መወጣት እንደሚቻል ለማወቅ በርካታ መንገዶችን ተጠቅሜያለሁ። ይህንን በማሳካቴ ደግሞ በጣም ደስተኛ ነኝ።"

ከስደተኛ ቤተሰብ የተገኙት ሉዊስ ወላጆቻቸው ፋብሪካ ውስጥ ነበር የሚሰሩት። በዚህ ምክንያት እርሳቸው ልጅ እያሉ የትምህርት ሙሉ ወጪያቸውን ቤተሰቦቻቸው መሸፈን አይችሉም ነበር። ነገር ግን በስተርጅናም ቢሆን ይህን እድል አግኝተውታል።

ሉዊስ እንደሚሉት ሴት መሆናቸው በራሱ በርካታ ነገሮችን ከባድ አደርገውባቸው ነበር።

ሴቶች ሁሌም ቢሆን በእርግዝና፣ ልጆችን መንከባከብ እና ቤተሰባዊ ኃላፊነቶች ምክንያት ወጥ የሆነ የትምህርትም ሆነ የሥራ ህይወት እንዳይኖራቸው ያደርጋሉ። "ለዚህም ነው ካረጁም በኋላ ቢሆን ሰዎች ትምህርት መማር እንደሚችሉ የሚያሳይ ምርምር የሰራሁት።"

ሉዊስ እንደሚሉት የምርምራቸው ዋነኛ ዓላማ በእድሜ የገፉ ሰዎች ወደ ትምሀርት ቤት መግባት የለባቸውም አልያም አይችሉም የሚለውን አስተሳሰብ መስበር ነው።

ኢንዶኔዢያ፡ "አሁን ላይ መማር ከቻልን መቼም ቢሆን ማቆም የለብንም"

የ87 ዓመቱ ላኦዴ ሙሃማድ ሲዲክ ከቀድሞ ተማሪያቸው (ግራ) እና ከልጅ ልጃቸው ጋር (ቀኝ)

የፎቶው ባለመብት, La Ode Muhammad Sidik

የምስሉ መግለጫ, የ87 ዓመቱ ላኦዴ ሙሐማድ ሲዲክ ከቀድሞ ተማሪያቸው (ግራ) እና ከልጅ ልጃቸው ጋር (ቀኝ)

ከሁለት ዓመታት በፊት የ87 ዓመቱ ላኦዴ ሙሐማድ ሲዲክ በኢንዶኔዢያዋ ደሴት ሱላዌሲ ከሚገኘው ቡቶን ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል።

ለእርሳቸው ይህ ትልቅ ህልም ነበር። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ከዚህ በኋላ በትምህርቱ ዓለም መቀጠል ነው ህልማቸው።

የቀድሞው መምህር ሁሌም ቢሆን ዩኒቨርሲቲ ገብቶ መማርን ይመኙ ነበር። ነገር ግን ልጆቻቸውን ለማስተማር ሲሉ ይህንን ህልማቸውን ወደ ጎን በማለት የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል።

በፈረንጆቹ 2012 ላይ ግን አንደኛው ልጃቸው ኮሌጅ ገብተው እንዲማሩ ይመክራቸዋል። የዚያን ጊዜ የ78 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ነበሩ። ነገር ግን ትምህርታቸውን በጀመሩ ሁለተኛው ዓመት በጠና ታመው ትምህርቱን መቀጠል ፈታኝ ሆነባቸው።

"ለአንድ ዓመት ተኩል ያክል በጠና ታምሜ ነበር"

ነገር ግን ላኦዴ ሙሃማድ እንዲህ በቀላሉ እጅ የሚሰጡ ሰው አይደሉም። በዚያ ላይ ደግሞ ቤተሰቦቻቸው በከፍተኛ ሁኔታ ያበረታቷቸውና ይደግፏቸው ነበር።

ከህመማቸው አገግመው ትምህርታቸውን ቀጠሉ። ከልጅ ልጆቻቸው አንደኛው የሆነው ሲናገር አያቱ አንድም ቀን ትምህርት ከበደኝ ብለው እንደማያውቁ ገልጿል።

"በጠና ቢታመም እንኳን ሁሌም ወደ ትምህርት ቤት ስለመሄድ ብቻ ነው የሚያስበው። መቼም ቢሆን መቅረት አይፈልግም።"

ታዲያ ከሰባት ዓመታት በኋላ ላኦዴ ሙሐማድ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ማግኘት ችለዋል።

"ከቀድሞ ተማሪዎቼ አንዱ በዩኒቨርሲቲው መምህር ነው። እሱ በጣም ረድቶኛል። ሁሉንም በጣም ማመስገን እፈልጋለው። ጥሩ ዜጎች እንዲሆኑ አስተምሬያቸው ነበር። አሁን ደግሞ እነሱ መልሰው ትምህርት እየሰጡኝ ነው። በጣም ደስተኛ ነኝ።"

"መማር እስከቻልን ድረስ መቼም ቢሆን ማቆም የለብንም። ገንዘቡና ጊዜው ካለኝ አሁንም ማስተርስ ዲግሪዬን መቀጠል እፈልጋለው።"