ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል በኢትዮጵያ መንግሥት ተጥሎበት የነበረው እገዳ ተነሳለት

የፎቶው ባለመብት, Ncr
ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል የተባለው የእርዳታ ድርጅት ከወራት በፊት በኢትዮጵያ መንግሥት የተጣለበት እገዳ እንደተነሳለት አስታወቀ።
ከተቋቋሙበት አላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል በሚል ከታገዱት ሦስት የእርዳታ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል ለአምስት ወራት ተጥሎበት የነበረው እገዳ እንደተነሳለት ከመንግሥት ተገልጾለታል።
በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የረድዔት ድርጅቶች የሚመዘግበውና የሚቆጣጠረው መንግሥታዊው ተቋም፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ባለፈው ዓመት ማብቂያ አካባቢ ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል እና በሌሎቹ ላይ እገዳ መጣሉን አስታወቆ ነበር።
ኤጀንሲው ለእገዳው በሰጠው ምክንያት በሦስቱ የውጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይ ባደረገው ክትትል መሠረት ድርጅቶቹ ከተቋቋሙለት አላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው ለሦስት ወራት እግድ የተጣለባቸው ሲሆን በተከታይነትም እግዱ ለሁለት ወራት ተራዝሞ ቆይቷል።
ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል እንደሚለው እገዳው የተጣለበት በአገሪቱ ውስጥ ስላላው የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎትና አቅርቦት ዙሪያ በሚያቀርበው ጥሪና በሌሎች ከአስተዳዳራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዙ የድርጅቱ ሥራዎች ምክንያት መሆኑን የእገዳውን መነሳት ባሳወቀበት መግለጫው አመልክቷል።
ጥቅምት ወር ላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የጣለውን እገዳ ባራዘመበት ጊዜ ጥያቄዎችን ማንሳቱን መግለጫው አመልክቶ ካውንስሉም ምላሽና ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ ከቀረቡበት አብዛኞቹ ክሶች ነጻ በመሆኑ ካለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ እገዳው መነሳቱን ገልጿል።
ነገር ግን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ እገዳውን ሲያነሳ ሁለት አስተዳደራዊ ጉዳዮችንና ከሚያቀርበው ጥሪ ጋር በተያያዘ "ጥብቅ ማስጠንቀቂያ" እንደተሰጠው ኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል አመልክቷል።
ድርጅቱ ዋና ፀሐፊ ያን ኢግላንድ "በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች በምናከናውነው የሰብአዊ እርዳታ ሥራ ላይ ተጥሎ የነበረው ጊዜያዊ እገዳ በመነሳቱ እፎይታ ተሰምቶናል" በማለት ተናግረዋል።
ጨምረውም ድርጅታቸው በዓለም ዙሪያ እንደሚያደርገው ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥ በነጻነት ተንቀሳቅሶ የሰብአዊ እርዳታ ሥራውን ማከናወን እንደሚፈልግና ለዚህም መንግሥት በአስቸኳይ ፈቃድና ቪዛ እንደሚሰጣቸው ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስልን፣ የሆላንድ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን እና አል ማክቱም ፋውንዴሽን የተባሉ ሦስት የረድኤት ድርጅቶች ላይ የሦስት ወራት እገዳ እንደተጣለባቸው መንግሥት ገልጾ ነበር።
እገዳው በተጣለበት ጊዜ ከ250 ሺዎች በላይ ለሆኑ ሰዎች የትምህርት፣ የንጹህ ውሃ፣ የመጠለያ፣የምግብ እና የሕግ ድጋፍን ሲሰጥ እንደነበረ የገለፀው የኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል አሁን እገዳው ተነስቶለታል።
ነገር ግን ከኖርዌጂያን ሪፊዩጂ ካውንስል ጋር እገዳው የተጣለባቸው የሆላንድ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን እና አል ማክቱም ፋውንዴሽን በተመሳሳይ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ተፈቅዶላቸው እንደሆነ ከኤጀንሲውም ሆነ ከረድኤት ድርጅቶቹ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።














