የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር በእግዱ ዙሪያ መወያየቱን አስታወቀ

የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ ጃን ኢግላንድ

የፎቶው ባለመብት, YASUYOSHI CHIBA

ለተወሰኑ ወራት በኢትዮጵያ እንዳይንቀሳቀስ የታገደው የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር መወያየቱን አስታወቀ።

የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ ጃን ኢግላንድ በነሐሴ ወር አዲስ አበባን እንደጎበኙና ከፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውን ድርጅቱ በድረ-ገፁ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

ዋና ፀሐፊው ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ጋር ገንቢ የሚባል ውይይት እንደነበራቸው ተገልጿል።

በውይይታቸውም በድርጅቱ ላይ የተጣለውን እግድ፣ የሥራ ፈቃድ፣ የሠራተኞች ደመወዝ፣ ወሳኝ የህይወት አድን ፕሮግራሞችን ማሰጀመር የመሳሰሉ ተዛማጅ ጉዳዮችን አንስተዋል ተብሏል።

"ለሰብዓዊ እርዳታዎች ነፃ፣ ገለልተኛ የሆነ ምላሽ ለመስጠት ያለንን ቁርጠኝነት ነግረናቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት ያለንን ፍላጎትና ከባለሥልጣናቱም ጋር ገንቢ በሆነ ግንኙነት ለመቀጠል ያለንን ፍላጎትም አሳውቀናል" በማለት የድርጅቱ የአጋርነት እና የፖሊሲ ዳይሬክተር የሆኑት ኦሌ ሶልቫንግ መናገራቸው በድረ-ገጹ ሰፍሯል።

የኖርዌይ የስደተኞች ካውንስልን ጨምሮ ሦስት የረድዔት ድርጅቶች ለሦስት ወራት የታገዱት ሐምሌ 23/2013 ዓ.ም ነበር።

የሆላንድ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን፣ የኖርዌይ የስደተኞች ካውንስልን እና አል ማክቱም ፋውንዴሽን ከተቋቋሙለት አላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው እግዱ መተላለፉን የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አስታውቆ ነበር።

ኤጀንሲው "ሦስቱ ድርጅቶች ከተቋቋሙለት ዓላማ ውጪና የአገርን ጥቅም በሚጻረር መልኩ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው" እንዲታረሙ በተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም ሊያስተካክሉ ስላልቻሉ አጠቃላይ ምርመራ ተደርጎ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የድርጅቶቹ እንቅስቃሴ ለሦስት ወራት መታገዱን ገልጿል።

"አስፈላጊ የሆነው የሰብዓዊ ሥራችንን በፍጥነት ለማስቀጠል ያስችለን ዘንድ፤ ባለሥልጣናቱ እግዱን ያነሱታል በሚል ተስፋ የምናደርገውን ውይይት እንቀጥላለን" በማለት አሌ ሶልቫንግ ተናግረዋል።

አክለውም "እግዱ በተራዘመ ቁጥር በሠራተኞቻች፣ በአጋሮቻችንና በችግር ላይ ባሉና በምንረዳቸው ሰዎች ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ መዘዝ ክፉኛ እያስጨነቀን ነው" ብለዋል።

ድርጅቱ ከአውሮፓውያኑ 2011 ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት፣ በንፁህ ውሃ እና የንፅህና መጠበቂያ ተቋማት፣ መጠለያ፣ ምግብ እና ሕጋዊ መታወቂያ ሰጥቷል።

በአውሮፓውያኑ 2020ም በስድስት ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልል፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ እና በሶማሌ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ 585 ሺህ ሰዎችን ማገዙ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም አንዳንድ እርዳታ ድርጅቶች ለህወሓት ኃይሎች ያልተፈቀዱ ድጋፎችን ለማድረግ ስለመሞከራቸው ማስረጃ አለ በማለት ስማቸው ያልተገለጹ ድርጅቶችን ሲወቅሱ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች ለትግራይ ተዋጊዎች ያደላሉ እንዲሁም ያስታጥቃሉ ማለታቸውን አደገኛ ነው ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

ኃላፊው የእርዳታ ድርጅቶች ላይ የተቃጣው "መሠረተ ቢስ ወቀሳ" ሊቆም ይገባል እንዲሁም የጅምላ ውንጀላዎች መሰንዘር ትክክል አይደለም ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቦ ነበር።

"ማስረጃ ካለ በማስረጃ ሊደገፉ ይገባል፤ እውነት ለመናገር ግን ይህ አካሄድ አደገኛ ነው" ማለታቸው የሚታወስ ነው።