ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ንብ እርባታ፡ በቺሊ ንብ አናቢዎች መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ለመጠየቅ ተቃውሞ አካሄዱ
በደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ቺሊ የሚገኙ ንብ አናቢዎች መንግሥት ኢንደስትሪያቸውን እንዲደግፍ ለመጠየቅ ያካሄዱትን ተቃውሞ ተከትሎ አራት ንብ አናቢዎች ታሰሩ።
ንብ አናቢዎቹ ተቃውሟቸውን ያሰሙት በአገሪቷ መዲና ሳንቲያጎ በሚገኝ የፕሬዚደንቱ ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት ነበር።
ንብ አናቢዎቹ ባካሄዱት ተቃውሞ የገጠማቸውን ችግር ለማስረዳት 10 ሺህ የሚጠጉ ንቦችን የያዙ 60 የሚሆኑ የንብ ቀፎዎችን በቤተ መንግሥቱ ፊት ለፊት በማስቀመጥ ፖሊስ ሰልፉን እንዳይበትን ሲከላከሉ ነበር።
ሰባት የፖሊስ መኮንኖችም ዋና መንገዱን ለመዝጋት በተቃዋሚዎቹ የተቀመጡ ቀፎዎችን ለማንሳት ሲሞክሩ በንብ ተነድፈዋል።
በቺሊ ለረዥም ጊዜ የዘለቀው ድርቅ በንብ እርባታ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ሲሆን የንቦች የምግብ ምንጭ በሆኑት እንደ አበባ እና ሌሎች ሰብሎች ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል።
ከተቃዋሚዎቹ መካከል አንዱ የንቦች መንጋ ሞት ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም አሳዛኝ እንደሆነ ለጋዜጠኞች ተናግሯል።
አንድ የንብ መንጋ 7 ሺህ የሚጠጉ ሠራተኛ ንቦችንና ከአንድ በላይ ንግሥት ንቦችን የሚይዝ ነው።
በመሆኑም ተቃዋሚዎቹ መንግሥት የማር ዋጋ ላይ ማሻሻያ እንዲያደርግ አሊያም ለማር አምራቾች ድጎማ እንዲያደርግ እንደሚፈልጉ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የግብርና ሚኒስቴር ባለሥልጣናት በድርቁ ሳቢያ ተቃዋሚዎቹ የገባቸውን ስጋት እንደሚጋሩት ገልጸው፤ ከፍተኛ የውሃ እጥረት ለገጠማቸው 20 ማኅበረሰቦች ለወራት እርዳታ ሲሰጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ተቃውሞው ከቀፎው የወጡ አንዳንድ ንቦች እንዲበሩ ምክንያት በመሆን ለመንገደኞች ሌላ ስጋት ፈጥሯል።
አንድ ግለሰብ "ይህ ለንብ አለርጅ ለሆኑ ሰዎች አደገኛ ነው። ሞትም ሊያስከትል ይችላል" ሲል ለጋዜጠኞች ተናግሯል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም ላይ ያለው የንቦች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል። ለዚህ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት መካካል ምቹ አካባቢ አለመኖር፣ ብክለት እና የፀረ ነፍሳት ኬሚካል አጠቃቀም ይገኙበታል።