ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሳንታንዴር ባንክ 130 ሚሊዮን ዩሮ ለደንበኞች በስህተት በተነ
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የፈረንጆች ገና ቀና ጠዋት የወረደላቸውን 'ሲሳይ' ሲመለከቱ ማመን አልቻሉም። ይህን 'ሲሳይ' የላከላቸው ደግሞ ሳንታንዴር የተሰኘው ባንክ ነው።
ባንኩ በስህተት ለ75 ሺህ ባለደብተሮች 130 ሚሊዮን ዩሮ ባለፈው ቅዳሜ እንደ ቅርጫ አድሏል።
የባንኩ ሠራተኞች አሁን ይህንን ገንዘብ ለማስመለስ ደፋ ቀና እያሉ ነው። ነገር ግን ጉዳዩን ከባድ ያደረገው ባንኩ ብሩን ያደለው በሌሎች ባንኮች ደብተር ውስጥ መሆኑ ነው ሲል ታይምስ ዘግቧል።
ስህተቱ የተከሰተው ለ2 ሺህ የንግድ አካውንቶች ሁሉት ጊዜ ክፍያ በመፈፀሙ ነው።
"ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታችን የጎላ ነው። ሳናስበው የደንበኞቻችንን ገንዘብ ለሌሎች ባለደብተሮች አድለናል" ሲል ባንኩ መግለጫ አውጥቷል።
ባንኩ ዩናይት ኪንግደም ውስጥ ካሉ ሌሎች ባንኮች ጋር በመተባበር የዘራውን ገንዘብ ለመሰብሰብ እንደሚሠራም ገልጧል።
ለሕትመት እየበቁ እንዳሉ ዘገባዎች ከሆነ አንዳንድ ደንበኞች ከቀጣሪዎቻቸው ሁሉት ጊዜ ክፍያ ደርሷቸዋል።
ነገር ግን አንደኛው ክፍያ የመጣው እነሱ አዘውትረው ከሚጠቀሙበት ባንክ ሳይሆን ሳንታንዴር ከተሰኘው ባንክ ነው።
ስሜን አደራችሁን እንዳትጠቅሱ ያለ አንድ የባንኩ የክፍያ ኃላፊ በዚህ ስህተት ምክንያት የባንኩ ሠራተኞች ገናን በቅጡ እንዳላከበሩ ለቢቢሲ ተናግሯል።
"የበዓል ቀን ግራ ተጋብቼ ነበር። ምክንያቱም በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ በስህተት አውጥቼ በተንኩ ብዬ አስቤ ስለነበር" ሲል ለቢቢሲ ሹክ ብሏል።
"ይህንን ስህተት በመፈፀሜ ሥራዬን ከማጣት አልፌ ሌላ ጣጣ ውስጥ የገባሁ መስሎኝ ነበር።"
ይህ ውስጥ አዋቂ ሳንታንዴር የተሰኘው ባንክ ሁለተኛው ክፍያ እንዴት እንደተፈፀመ አስረድተን ገንዘቡን ማስመለስ እንችላለን የሚለውን አልነገረንም ይላል።
"ብቻ ሁሉም ነገር ውጥንቅጡ ወጥቷል። እንዴት አድርገው ብሩን እንደሚሰበሰቡት እኔ አላውቅም" ይላል የክፍያ ኃላፊው።
ባንኩ ከሌሎች ባንኮች ጋር እየሠራሁ ነው ብሏል። ታይምስ እንደሚለው እኒህ ባንኮች ባርክሌይስ፣ ኤችኤስቢሲ፣ ናትዌስት፣ ኮ-ኦፕሬቲቭ እና ቨርጂን መኒ የተሰኙት ናቸው።
ሳንታንዴር እኒህ ከላይ የተጠቀሱት ባንኮች በስህተት የገባውን ገንዘብ ከደንበኞቻቸው ሰብስበው ይመልሱልኝ ይሆናል የሚል ተስፋ ሰንቋል።
ነገር ግን ሰዎች ገንዘቡ ከገባላቸው በኋላ ጥቅም ላይ አውለውት ከሆነ እንዴት ነው ሊመልሱት የሚችለው የሚለው አከራካሪ ሆኗል።
ሳንታንዴር 'የገና ሲሳይ' የወረደላቸውን ሰዎች ቀጥታ ደውሎ እባካችሁ ገንዘቤን መልሱልኝ ሊል እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል።