ቻይና የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾቿ እንዳይነቀሱ፣ የተነቀሱም እንዲያጠፉ አዘዘች

በቻይና የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የሚጫወቱ ሰውነታቸውን እንዳይነቀሱ፣ ተነቅሰውም ከሆነ እንዲያጠፉት የሚያዝ አዲስ መመሪያ ወጣ።

ይህ የቻይና ስፖርት የበላይ አስተዳዳሪ አካል ያወጣው መመሪያ እንደሚለው በአገሪቱ ብሔራዊ የእግርኳስ ቡድን እንዲሁም የወጣቶች ቡድን ውስጥ የተነቀሱ ተጫዋቾችን መመልመል "በጥብቅ የተከለከለ" ነው።

አስተዳደሩ እንዳለው ይህ እርምጃ "ለማኅበረሰቡ መልካም አርአያ" ይሆናልም ብሏል።

ዣንግ ሊንፔንግን ጨምሮ የቻይና እግር ኳስ ኮከብ ተጫዋቾች ከዚህ በፊት በሰውነታቸው ላይ ያለውን ንቅሳት እንዲሸፍኑ ተነግሯቸው ነበር።

ቻይና ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በተጫዋቾች ላይ ያሉ ንቅሳቶች በቴሌቪዥን መስኮቶች ላይ እንዳይታዩ ቁጥጥሯን አጥብቃለች። በዚህም ሳቢያ አንዳንድ ታዋቂ ተጫዋቾች በክንዳቸው ላይ ያለ ንቅሳትን ለመሸፈን እጅጌ ረጅም ያላቸው ከነቴራዎችን ለመልበስ ተገድደዋል።

የቻይና አጠቃላይ ስፖርቶች አስተዳደር ባወጣው መግለጫ፣ ለአገሪቱ ብሔራዊ ቡድን የሚጫወቱ ስፖርተኞች በሰውነታቸው ላይ ያለ ንቅሳትን "እንዲያስወግዱ ተነግሯቸዋል።"

"ልዩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ደግሞ፣ የቡድኑ አባላት ሲስማሙ በልምምድ እና በውድድር ጊዜ ንቀሳታቸውን እንዲሸፍኑ ይደረጋል" ብሏል።

በቻይና ባህል ንቅሳት ያለባቸው ሰዎች መገለል ይገጥማቸዋል። ቀደም ባሉት ጊዜያት በምሥራቅ እስያ ውስጥ ንቅሳትን ወንጀለኞችን እንደመለያ ምልክት ጥቅም ላይ ይውል የነበረ ሲሆን አሁንም ከተደራጁ ወንጀለኞች ጋር ይያያዛል። በተጨማሪም በአንዳንድ ጎሳዎች ላይ የኋላ ቀርነት ምልክት ተደርጎ ይታያል።

ንቅሳቶች በቻይና ገዢ ኮሚዩኒስት ፓርቲ በኩል ተቀባይነት ባይኖረውም፣ በቻይና ወጣቶች ዘንድ ግን በስፋት ተቀባይ እየሆነ ይገኛል።

የቻይና የመገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣሪ አካል ባለፈው ዓመት ንቅሳትን በሚመለከት "ጤናማ ያልሆኑ" ያላቸውን ገጽታዎች በሚመለከት ያለው ደንብ ጥብቅ አድርጓል።

በዚህም በቴሌቪዥንና በኢንተርኔት አማካኝነት የሚቀርቡ ታዋቂ ሰዎችና ስፖርተኞች ላይ በሚታዩ ንቅሳቶችና የፀጉር አሰራሮች በተመለከተ ክልከላዎችን ጥሏል። በአንዳንድ አጋጣሚዎች ምስላቸው እንዲደበዝዝ የተደረገበት ሁኔታም ነበር።

ባለፈው ወር ቻይና ውስጥ ሴት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሊያደርጉት የነበረው የእግር ኳስ ጨዋታ ፀጉራቸውን ቀለም የተቀቡ ተጫዋቾች በውድድሩ እንዲሳተፉ ስላልተፈቀደላቸው ግጥሚያው ተሰርዟል።

በወቅቱ የውድድሩ አዘጋጅ አውጥቶት ነበረው መግለጫ "በየትኛውም ደረጃ ያሉ ስፖርተኞች መነቀስ፣ ፀጉራቸውን ቀለም መቀባት፣ የተለያ የፀጉር አቆራረጥ ወይም ጌጥ ማድረግ የለባቸውም፤ ይህ ከሆነ ግን በውድድር ለመሳተፍ አይችሉም" ሲል አስታውቋል።