ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፕሬዝዳንት ፋርማጆ ከሥራ የታገዱት የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ተቃውሟቸውን አሰሙ
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ በሕገ ወጥ መንገድ መሬት በመቀራመት እጃቸው አለበት የተባሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ሁሴን ሮብሌን ከሥራ አግደዋል።
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ሁሴን ሮብሌ ፕሬዚዳንቱ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሞክረዋል በማለት የወነጀሏቸው ሲሆን በሥልጣናቸው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
ከዚያም አልፈው የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ትዕዛዝ መቀበል ያለባቸው ከፕሬዝዳንት ፋርማጆ ይልቅ ከእሳቸው እንደሆነም አሳስበዋል።
ለፕሬዚዳንቱ ታማኝ የሆኑ ወታደሮች ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌ በአገሪቱ ዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ወደሚገኘው ቢሯቸው መግባት አልቻሉም ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅርበት ያላቸው ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ የገቡ ሲሆን ይህም በሶማሊያ ተጨማሪ አለመረጋጋት እንዳያስከትል ስጋት ፈጥሯል።
በሶማሊያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ መሪዎቹ "ከጸብ ጫሪ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ እና የኃይል እርምጃዎችን እንዲያስወግዱ" አሳስቧል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ1991 የሶማሊያ የረዥም ጊዜ መሪ የነበረው ሲያድ ባሬ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ሶማሊያ ውጤታማ ማዕከላዊ መንግሥት ሳታገኝ ቆይታለች።
አገሪቱ በተለያዩ ጎራ በተሰለፉ ፖለቲከኞች እና በጎሳዎች መካከል ፈተና ውስጥ የምትገኝ ሲሆን ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ካለው አልሸባብ አማፅያን ጋር አገሪቱ እየተዋጋች ነው።
አሁን ሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ፋርማጆ የሥልጣን ጊዜ በይፋ ያበቃው በፈረንጆቹ የካቲት ወር ላይ ቢሆንም አዲስ ፕሬዝዳንት እንዴት እንደሚመረጥ በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ምርጫው ተራዝሟል።
የጎሳ መሪዎች የፓርላማ አባላትን የሚመርጡበት የተወሳሰበው የሶማሊያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ከኅዳር ወር ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን ከቀናት በፊት መጠናቀቅ ቢኖርበትም እሳካሁን አላለቀም።
ለምርጫው መስተጓጎል ፕሬዝዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርስ በእርሳቸው እየተወነጃጀሉም ነው።
ፕሬዝዳንት ፋርማጆ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የቀረበውን የሙስና ውንጀላ ለማጣራት የምርመራ ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌ ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር በመሆን በቅርቡ በሞቃዲሾ የሚገኘውን የአገሪቱ ጦር ንብረት የሆነውን መሬት ተገቢ ባልሆነ መንገድ በመጠቀም እና መቀራመት ተሳትፎ አላቸው ተብለው ቢከሰሱም እሳቸው ግን ክሱን አይቀበሉትም።
ፕሬዝዳንት ፋርማጆ ሮብሌን ከሥራ ካገዱ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በትዊተር ገጹ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ "እንደተለመደው" የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን እያከናወኑ መሆናቸውን አስፍሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በቅቡል የምርጫ ሂደት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር" ላይ ቁርጠኝነት እንዳላቸው ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብሌ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፕሬዚዳንቱ "በመንግሥት፣ በሕገ-መንግሥቱ እና በአገሪቱ ሕጎች ላይ" መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ እየሞከሩ ነው።
በሶማሊያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን በቀጥታ በተላለፈው መግለጫ ላይ "ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች ከመንግሥት... ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ትዕዛዝ እንዲቀበሉ አዝዣለሁ" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋጩት በፈረንጆቹ ሚያዝያ ወር ላይ ፕሬዝዳንት ፋርማጆ የሥልጣን ዘመናቸውን ባራዘሙበት ወቅት ሲሆን በዚህም ምክንያት በሞቃዲሾ በሁለቱ ታማኝ ወታደሮች መካከል ውጥረት ተፈጥሮ ነበር።
ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለሥልጣናትን የመሻር እና የመሾም ሥልጣናቸውን ሲነጥቋቸው ደግሞ በሁለቱ መሪዎች መካከል ደግም ውጥረት ነግሷል።