ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የደቡብ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ በ90 ዓመታቸው አረፉ
የደቡብ አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ በ90 ዓመታቸው አረፉ።
ዴዝሞንድ ቱቱ በደቡብ አፍሪካ የጨቋኙን አፓርታይድ ስርዓት እንዲወገድ የታገሉና የኖቤል የሰላም ተሸላሚም ነበሩ።
የሊቀ ጳጳሱን ከዚህ አለም በሞት መለየት አስመልክቶም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ አረጋግጠው መግለጫ አውጥተዋል።
የእሳቸው ማረፍ "ነፃ የወጣች ደቡብ አፍሪካን በውርስ ያበረከቱልን ያ ድንቅ ትውልድ አካል ስንብት አንድ ምዕራፍ መሆኑን ማሳያ ነው" ብለዋል ፕሬዚዳንቱ
ዴዝሞንድ ቱቱ በአገራቸው ደቡብ አፍሪካም ሆነ በተለያዩ አገራት ስመ ጥር የሆኑና በሰላም ምልክት ከሚታወቁ ግለሰቦች መካከል አንዱ ነበሩ።
በደቡብ አፍሪካ አናሳ ነጭ መንግሥት ሲተገበር የነበረውንና በጥቁሮች ላይ ከፍተኛ ጭቆና፣ ግፍና አድሏዊነት በፖሊሲ ደረጃ የጫነውን የአፓርታይድ ስርዓት በመቃወም ከነበረው ትግል ጀርባ አንቀሳቃሽ ግለሰቦች አንዱ መሆናቸውም ይወሳል።
በትግሉም ከአውሮፓውያኑ 1948-1991 ድረስ ቆይተዋል።
የአፓርታይድ ስርዓትን ለማስወገድ በተደረገው ትግል ላበረከቱት ሚና በአውሮፓውያኑ 1984 የሰላም የኖቤል ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ዴዝሞንድ ቱቱ "አርዓያ የሚሆኑ መንፈሳዊ መሪ፣ ፀረ-አፓርታይድ ታጋይና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች" ናቸው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም " አቻ የማይገኝላቸው አርበኛ፤ እምነት በስራ ካልታገዘ ትርጉም የለውም የሚለውን የመፅሃፍ ቅዱስ ግንዛቤ ትርጉም የሰጡ የመርህ እና ተግባራዊነት መሪ" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
"ለየት ያለ የአምሮ ልዕልና ያላቸው፣ ለትግሉ ታማኝ እና በአፓርታይድ ሃይሎች ላይ የአይበገሬነት ስሜት ያሳዩ፣ በአፓርታይድ አገዛዝ ግፍ፣ ኢ-ፍትሃዊነት፣ ጭቆናንና በደልን ላዩ ርህራሄንና እንክብካቤን የሚያሳዩ ነበሩ። በአለም ላይ ጭቆናን እያዩ ላሉም ርህራሄያቸውን ያሳዩ ነበር" በማለት መስክረዋል።