የኢትዮጵያ ኃይሎች ሰቆጣን ተቆጣጥረው ወደ አላማጣ እና ኮረም እያመሩ መሆናቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Government Communication Service/fb
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና አጋሮቹ በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር ወደ አላማጣና ኮረም እያመሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ረቡዕ ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች በቆቦ ግንባር በአንድ በዋጃና ጥሙጋ በኩል ወደ አላማጣ ከተማ እንዲሁም በተኩለሽ በኩል ወደ መረዋና ኮረም እያመሩ መሆናቸውን ገልጿል።
በተጨማሪም ለረጅም ጊዜ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የቆየችውን በአማራ ክልል የዋግ ኽምራ ብሔሰብ ዞን ዋና ከተማ፣ ሰቆጣን ጨምሮ አብዛኛውን አካባቢዎች ከአማጺያኑ በማስለቀቅ አካባቢዎቹ በመንግሥት ቁጥጥር ስር መግባታቸው ተነግሯል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የህወሓት ቡድንን ለማሳደድ ትግራይ ውስጥ ሁሉን አቀፍ ወታደራዊ ዘመቻ የማካሄድ ፍላጎት እንደሌለው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለውጭ አገር አምባሳደሮች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ገልጸው ነበር።
ጨምረውም ከዚህ በኋላ ህወሓት ምንም አይነት ጥቃት ለመፈጸም እንዳይችል ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ መንግሥታቸው እንደሚያደርግ እና የአገሪቱን የግዛት አንድነት የማስከበር ኃላፊነቱን ለመወጣት ትግራይን ጨምሮ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የፈደራሉን ሠራዊት የማሰማራት መብቱን እንደሚያስከብር ገልጸዋል ነበር።
ካለፈው ኅዳር ወር ወዲህ መንግሥት ባካሄዳቸው ከፍተኛ ተከታታይ ወታደራዊ ዘመቻዎች በህወሓት ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ለማስለቀቅ የቻለ ሲሆን፣ የቡድኑ መሪዎች ግን ስልታዊ ውሳኔ ነው ሲሉ ቆይተዋል።
ከቀናት በፊት ደግሞ የህወሓት መሪዎች ኃይሎቻቸውን ከአፋርና ከአማራ ክልል እያስወጡ ያሉት ለሰላማዊ መፍትሔ እድል ለመስጠት ነው ቢሉም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ከባድ ወታደራዊ ሽንፈት ስላጋጠማቸው መሆኑን ገልጿል።
ባለፈው ዓመት በትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክሎች የተስፋፋው ጦርነት ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ ተባብሶ ከሰሜን ወሎ ወደ ደቡብ ወሎ በመሻገር፣ የደሴና የኮምቦልቻ ከተሞች በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ገብተው እንደነበር ይታወሳል።
ከዚህም በተጨማሪ አማፂዎቹ ጥቃታቸውን ወደ ሰሜን ሸዋ አስፋፍተውም ነበር።
የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልል በመግባት ዘመቻ በማካሄዳቸው በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የተለያዩ ቦታዎችን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ለማቅናት ፍላጎት እንዳለቸው ሲገልጹ ቆይተው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎም በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ለማስለቀቅ ውጊያዎች ተጠናክረው ሲካሄዱ ቆይተዋል።
ከሳምንታት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መዝመት ተከትሎ የአማጺያኑ ግስጋሴ ከመገታቱ በተጨማሪ ይዘዋቸው ከነበሩ የአፋርና የአማራ ክልል አካባቢዎች ለቀው ለመውጣት ተገደዋል።
በዚህ የማጥቃት ዘመቻ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከልዩ ኃይልና ከሚሊሻው በተጨማሪ የአገሪቱ አየር ኃይል የተሳተፈ መሆኑ ተገልጿል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ትግራይ ውስጥ ሲካሄድ ቆይቶ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ከክልሉ ካስወጣ በኋላ ነበር የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመዝለቅ ጥቃት የከፈቱት።
በዚህም ሳቢያ በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር እስከ ሰሜን ሸዋ ለመድረስ ችለው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ በኅዳር ወር የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት፣ ከአፋርና ከአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች እንዲሁም ሚሊሻዎች ጋር በመቀናጀት ባካሄዱት የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የህወሓት ኃይሎች ከአፋር ክልል ሙሉ ለሙሉ እንዲሁም ከሰሜን ወሎ ዞን ሙሉ ለሙሉ ለማስወጣት መቻላቸው ተገልጿል።















