ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጦር ግንባር መልስ የመጀመሪያ የውጭ ጉዞ የቱርክ-አፍሪካ ጉባኤ

የፎቶው ባለመብት, PM Office
አርብ ታኅሣሥ 08/2014 ዓ.ም ወደ ቱርክ ኢስታንቡል ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እየተካሄደ ባለው ሦስተኛው የቱርክ አፍሪካ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ጽህፈት ቤታቸው በማኅበራዊ ገጹ አስታውቋል።
ጉባኤው ላይ ለመሳተፍ የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆን ጨምሮ በርካታ የአህጉሪቱ መሪዎች ወደ ኢስታንቡል ማቅናታቸው ተዘግቧል።
በጉባኤው ላይ ከ30 በላይ የአፍሪካ አገራት መሪዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሳምንታት በፊት ከአማጺያኑ ጋር የሚደረገውን ፍልሚያ በጦር ግንባር በመገኘት እንደሚመሩ አሳውቀው ወደ ጦር ግንባር ከዘመቱ በኋላ ያደረጉት ይህ የመጀመሪያው የውጭ አገር ጉዟቸው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል የደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን ጨምሮ በርካታ ቁልፍ ቦታዎች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ካስታወቁ በኋላ "የመጀመሪያው የዘመቻ ምዕራፍ ተጠናቋል" በማለት ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውን አስታውቀው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጉባኤው ጎን ለጎን እርሳቸውና ልዑካቸው ከፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማካሄዳቸውን ትናንት በማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
"የሁለቱ አገራት ታሪካዊ ግንኙነት ሁሌም በመከባበር ላይ የተመሠረተ ነው። ትብብራችን በገንቢ ተሳትፎ ላይ በመመስራት ይቀጥላል" ብለዋል ባሰፈሩት ጽሁፍ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬዝዳንት ኦርዶዋንንም ጉባኤውን በማስቀጠላቸው አመስግነዋቸዋል።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን በተለያየ ጊዜ አገራቸው ለኢትዮጵያ የትኛውንም አይነት ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጻቸው ይታወሳል።
በኮቪድ ምክንያት ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ የነበረውና ትናንት አርብ የተጀመረው የቱርክ አፍሪካ ጉባዔ ዛሬ ቅዳሜ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ቱርክ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ካላቸው አገራት መካከል አንዷ ስትሆን የጨርቃ ጨርቅ እና የኤሌክትሪክ ማስተላላፊያ ገመዶች ማምረቻዎችን ጨምሮ የቱርክ ኩባንያዎች 2.5 ቢሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ ፈሰስ ማድረጋቸውን ከዚህ ቀደም የቱርኩ ዜና ወኪል አናዱሉ ዘግቧል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ቱርክ ማቅናታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በወቅቱም ሁለቱ አገራት የመከላከያን ጨምሮ ሌሎች የትብብር ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት ቱርክ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት ለማብቃት አስተዋጽኦ ሊኖራት እንደሚችል የሚታመን ሲሆን፤ የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን በቅርቡ ከጎበኟቸው አገራት መካከል ቱርክ አንዷ ናት።
ቱርክ በሰሜን አፍሪካና በአፍሪካ ቀንድ ካሉ አገራት ጋር የጠነከረ ግንኙነት ያላት ስትሆን የሶማሊያ መንግሥትን በመደገፍ ቁልፍ ሚና ያላት አገር ናት።
በሊቢያ ፖለቲካ ውስጥም ተደማጭ ስትሆን ጎረቤት አገር ግብፅ ቱርክ በሊቢያ ውስጥ ባላት ሚና ደስተኛ ካለመሆኗ የተነሳ በተለያዩ ጊዜያት ዲፕሎማሲያዊ አተካራ ውስጥ ሲገቡ ቆይተዋል።
ከጎረቤት አገር ሱዳን ጋርም መልካም ግንኙነት ያላት ቱርክ ጄነራል አል ቡርሐን ከወራት በፊት በቱርክ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የድንበር ውዝግብን በተመለከተም ሱዳን የቱርክን አሸማጋይነት እንደምትቀበል ገልጻ ነበር።
ቱርክ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአውሮፓ አማካይ ስፍራ ላይ የምትገኝ ሲሆን ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ ነች።














