በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት የጂቡቲን የ20 ዓመታት እድገት ሊያሳጣ እንደሚችል ተገለጸ

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ከአንድ አመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነት የአፍሪካ ቀንድ አጎራባቿ ለሆነችው ጂቡቲ የ20 ዓመታት የኢኮኖሚ እድገት ሊያሳጣት የሚችል አደጋ መደቀኑ ተገለጸ።

የጂቡቲ የገንዘብ ሚኒስትር ኢልያስ ሙሳ ዳዋሌህ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጦርነቱ እየተካሄደ ባለበት ባለፉት አስራ ሁለት ወራት አገራቸው ግማሽ ያህል ብሔራዊ ሀብቷን ወይም 1.7 ቢሊዮን ዶላር አጥታለች፤ ይህም ገቢ በመቀነሱ እና ሥራዎች በመጥፋታቸው መሆኑም ተነግሯል።

"አሁን የሚያሳስበን የ20 ዓመታት ጠንካራ ሥራ እንዲሁም ከኢትዮጵያ እስከ ጂቡቲ ያለው የቀጠናው ልማት ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ይህም የተከሰተው የዚያ ግጭት መነሻ ሳንሆን ነው። ጂቡቲ ሁሌም ለሰላም አፅንኦት ትሰጣለች። ቀጣናውም ሆነ ጂቡቲ ይህንን ጦርነት አይችሉትም" ብለዋል የገንዘብ ሚኒስትሩ።

አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ጂቡቲ የተለያዩ ችግሮችን እየተጋፈጠች መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ በጦርነት የሚመጣ ዳፋ ተጨማሪ ተግዳሮት መሆን የለበትም ብለዋል።

"የሰው ልጅ እየተጋፈጣቸው ካሉ ፈታኝ ሁኔታዎች በላይ አላስፈላጊ ጫና ሊደረስበት አይገባም። ይህ ጦርነት በቅርቡ እንዲያበቃ በጽኑ እንጸልያለን። እርስ በርስ ከመዋጋት የተሻሉ ነገሮች ማድረግ እንችላለን" ብለዋል ሚኒስትሩ ከቢቢሲ አፍሪካ ቢዝነስ ጋር በነበራቸው ቆይታ።

በአንበጣ ወረራ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያቶች እየተንገታገተ ለነበረው የጂቡቲ ምጣኔ ሀብት ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው ግጭት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የአቅርቦት ሰንሰለት መቆራረጥ አስከትሏል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ አሸቆልቁሎ ወደ 20 በመቶ ወርዷል።

ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የአዲስ አበባ የሸቀጥ ዕቃዎች በጂቡቲ ወደብ በኩል የሚያልፉ ሲሆን ይህ ለአገሪቱ ከ1.5 እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኝላታል።

ጂቡቲና ኢትዮጵያም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን በማፍሰስ 757 ኪሎሜትር የባቡር መስመርን ጨምሮ ኢትዮጵያን በቀጥታ ከባሕር ወደቡ ጋር ማገናኘት የሚያስችል መንገዶችንም ዘርግተዋል።

ነገር ግን እየተካሄደ ላለው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ ካልተገኘ እነዚህ ሁሉ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባሉ የሚል ስጋት አለ።