አርሜኒያ እና አዘርባጃን ድንበር ላይ ወታደሮች ተገደሉ

በርከት ያሉ የአርሜኒያ ወታደሮች አዘርባጃን አዋሳኝ ድንበር ላይ ተገደሉ፡፡

እንደ አርሜኒያ ገለጻ ወታደሮቿ የተገደሉት በአዘርባጃን ወታደሮች ነው፡፡ አዘርባጃን በበኩሏ በዚህ ግጭት ሁለት ወታደሮቼ ቆስለውብኛል ስትል አርሜኒያን ከሳለች፡፡

ከሰሞኑ በሁለቱ አገሮች መካከል መጠነኛ ግጭት በድንበር አካባቢ መቀስቀሱ ተሰምቷል፡፡

ሆኖም ትናንት ማክሰኞ ሩሲያ መሀል ገብታ የጦር ማቆም ስምምነት እንዲፈርሙ አድርጋለች ተብሏል፡፡

ባለፈው ዓመት ሁለቱ አገራት ናጎርኖ ካራባህ በሚባል ግዛት የይገባኛል ጥያቄ በቀሰቀሱት ጦርነት የ6ሺህ ወታደሮች ሕይወት ማለፉ አይረሳም፡፡

በጦርነቱ ማብቂያ በቱርክ የሚደገፉት የአዘርባጃን መከላከያ አባላት የዚህን አወዛጋቢ ግዛት አብዛኛውን ክፍል በእጃቸው አስገብተዋል፡፡

ይህ አወዛጋቢ ግዛት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአዘርባጃን እንደሆነ የሚያውቅ ቢሆንም አርሜኒያ የኔ ነው በሚል ወደ ጦርነት ገብታ ነበር፡፡

ማክሰኞ ዕለት የሩሲያ የጸጥታና ደኅንነት አጋር የሆነችው አርሜኒያ፣ ሩሲያን ከአዘርባጃን ወረራ እንድትታደጋት ተማጽናታለች፡፡

ይህ ጥሪ ከቀረበ ከሰዓታት በኋላ ሩሲያ፣ አርሜኒያንና አዘርባጃንን ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ አግባብታለች፡፡

ይሁንና አዘርባጃን በዚህ ጉዳይ ላይ በይፋ ያለችው ነገር የለም፡፡

አርሜኒያ በብዛት ሕዝቧ የክርስትና እምነት ተከታይ ሲሆን አዘርባጃን በስፋት የእስልምና እምነት ተከታይ ሕዝብ ነው ያላት፡፡

ሩሲያ የሁለቱም አገሮች አጋር ስትሆን ከአርሜኒያ ጋር በተለይ የጸጥታ ትብብር ስምምነት አላት፡፡ ቱርክ በበኩሏ አዘርባጃንን በይፋ ትደግፋለች፡፡

በሰሞኑ ግጭት በትንሹ 15 የአርሜኒያ ወታደሮች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ይገመታል፡፡

አርሜኒያና አዘርባጃን ለ44 ተከታታይ ቀናት ከባድ የሚባል ውጊያ ያደረጉት ባለፈው ዓመት ነበር፡፡

ሁለቱ አገሮች የታላቋ ሶቪየት ኅብረትን የመጨረሻ ዘመን አካባቢ በታሪክ እጅግ ደም አፋሳሽ ጦርነት ያደረጉ ሲሆን ከሁለቱም ወገን በአስር ሺዎች ተገድለዋል፡፡