ፋይዘር የኮሮናቫይረስ ማከሚያ መድኃኒቱን ታዳጊ አገራች እንዲያመርቱት ፈቀደ

ፋይዘር በሙከራ ደረጃ ያለውን የኮሮናቫይረስ ማከሚያ እንክብል መድኃኒቱን ታዳጊ አገሮች እንዲሠሩት እና እንዲያከፋፍሉት ፈቀደ።

የአሜሪካው መድኃኒት አምራች ፋይዘር በ95 ታዳጊ አገራት እንክብል መድኃኒቱ እንዲመረት የተስማማው የተባበሩት መንግሥታት ከሚደግፈው ሜድስንስ ፔሸንት ፑል ድርጅት ጋር በመጣመር ነው።

ድርጅቱ የኮሮናቫይረስ ማከሚያ መድኃኒቱን ከሠራ በኋላ 53 በመቶ ለሚሆነው የዓለም ሕዝብ ያዳርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ስምምነቱ እንደ ብራዚል ያሉ በከፍተኛ ሁኔታ ቫይረሱ የተስፋፋባቸው አገራትን አያካትትም።

መድኃኒቱ ለሕመም ተጋላጭ የሆኑ ጎልማሶች በጽኑ በሽታ እንዳይያዙ እንደሚከላከል ፋይዘር አስታውቋል።

መድኃኒቱ በታዳጊ አገራት እንዲመረት መፍቀዱ "የመድኃኒቱን ተደራሽነት ያሰፋዋል" ሲል ገልጿል።

በታዳጊ አገራት ከሚመረተው መድኃኒት ፋይዘር የባለቤትነት (ሮያሊቲ) ክፍያ አይወስድም። ወረርሽኙ ለዓለም አስጊ ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ በሁሉም አገራት ትርፍ እንደማይሰበስብም ይፋ አድርጓል።

ፋይዘር ለኮቪድ-19 ማከሚያ እየሠራ ያለው ፓክሎቪድ የተባለ መድኃኒት ነው። ይህም በከፍተኛ ሁኔታ ለሕመም ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ሞትና ሆስፒታል የመግባት እድልን በ89 በመቶ ይቀንሳል ተብሏል።

የሜድስንስ ፔሸንት ፑል ኃላፊ ቻርልስ ጎሬ እንዳሉት መድኃኒቱ በታዳጊ አገራት እንዲመረት ፍቃድ መሰጠቱ መልካም ነው።

"ይህ መድኃኒት በተለይም አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ሕይወት ያድናል" ብለዋል።

መድኃኒቱን እንዲሠሩ ፈቃድ ካገኙ አገራት አብዛኞቹ በአፍሪካ እና እስያ ይገኛሉ።

እንደ ብራዚል፣ ቻይና፣ ሩስያ፣ አርጀንቲና እና ታይላንድ ያሉ ክፉኛ በወረርሽኙ የተጎዱ አገራት በስምምነቱ አልተካተቱም።

የኮሮናቫይረስ ሕክምና እንዲሁም ክትባቱን ተደራሽ ለማድረግ ይህ እርምጃ በቂ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ተችተዋል።

ፋይዘርን ጨምሮ ሌሎችም የኮቪድ-19 ክትባት አምራቾች የባለቤትነት መብታቸውን አንስተው፤ ክትባቱ በሌሎች አገራት እንዲመረት ፈቃድ እንዲሰጡ ቢጠየቁም አሻፈረኝ ብለዋል።

ዶክተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ ባወጣው መግለጫ፤ ፋይዘር ለታዳጊ አገራት የሰጠው ፈቃድ የኮሮናቫይረስ መድኃኒት በመላው ዓለም እንዲደርስ እንደማይረዳ ተችቷል።

"ወረርሽኙን መግታት ከፈለግን የኮሮናቫይረስ ማከሚያ መድኃኒት ለሁሉም ሰው፣ በሁሉም አገር መዳረስ አለበት" ሲሉ የድርጅቱ የሕግ አማካሪ ዩአንክዮንግ ሁ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም መርክ የተባለው መድኃኒት አምራች ድርጅት ሞልኑፒራቪር የተባለ የኮሮናቫይረስ መድኃኒቱ ከሜድስንስ ፔሸንት ፑል ጋር በጥምረት ለማምረት ተስማምቷል።