ኬንያውያን ፖሊሶች በዩኬ የንጉሣውያን ቤተሰብ አባል ሞት ምክንያት እስር ተፈረደባቸው

በኬንያዋ የባሕር ዳርቻ ከተማ ሞምባሳ አቅራቢያ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በፖሊስ እጅ እያለ ህይወቱ ያለፈው የዩናይትድ ኪንግደሙ (ዩኬ) የንጉሣውያን ቤተሰብ አባል ሞት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ አራት ኬንያውያን ፖሊሶች እስር ተፈረደባቸው።

አሌክሳንደር ሞንሰን በቁጥጥር ስር የዋለው በአውሮፓውያኑ 2012 ነበር።

በያዝነው ሳምንት በፖሊሶቹ ላይ የእስር ፍርድ የበየኑት ዳኛ ኤሪክ ኦጎላ፣ አሌክሳንደር ሞንሰን በአሰቃቂ ሁኔታ በፖሊሶች እጅ እንደተሰቃየ እና ከሞተም በኋላ በፖሊሶች የተቀነባበረ ዕፀ ፋርስ እንደተገኘበት ተገልጿል።

በ28 ዓመቱ የንጉሣውያን ቤተሰብ አባል ላይ የተፈጸመውን ነገር ፖሊሶች እንደደበቁም ዳኛው ተናግረዋል።

አሌክሳንደር ሞንሰን የሎርድ ኒኮላስ ሞንሰን ልጅ ሲሆን በሊንከንሻየር የቤተሰብ ርስት ወራሽ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2008 ከእናቱ ሂላሪ ሞንሰን ጋር አብሮ ለመኖር ነበር ወደ ኬንያ የሄደው።

አራቱ ፖሊሶች ከዘጠኝ እስከ 15 ዓመት የሚደርስ እስራት የተፈረደባቸው ቢሆንም ከእያንዳንዱ ፖሊስ ላይ ከአምስት እስከ ስድስት ዓመት የሚደርስ እስር ተቀንሷል።

ፖሊስ መጀመሪያ ላይ አሌክሳንደር ሞንሰን የሞተው የአደንዛዥ ዕፅ ከመጠን በላይ በመውሰዱ ነው ቢልም፣ ነገርግን በአውሮፓውያኑ 2018 በተደረገው ምርመራ በጭንቅላት ላይ በደረሰበት ጉዳት እንደሞተ ተረጋግጧል።

በተጨማሪም ምንም ዓይነት አደንዛዥ ዕፅ እንዳልወሰደም የምርመራ ሪፖርቱ አሳይቷል።

"አደንዛዥ ዕፅ አስከሬኑ ላይ ሆን ተብሎ እንዲገኝ የተደረገበት የአሟሟቱን ሁኔታ ለመደበቅ ነው" ሲሉ በሞምባሳ ፍርዱን የሰጡት ዳኛ አጎላ የተናገሩ ሲሆን አሌክሳንደር ሞንሰን በፖሊስ ጣቢያው ከመድረሱ በፊት በጥሩ ጤንነት ላይ ነበር ብለዋል።

አክለውም ግለሰቡን በአሰቃቂ ሁኔታ ያሰቃዩት አራቱ ፖሊሶች ናታሊ ቼጌ፣ ቻርልስ ዋንጎምቤ ሙኒሪ፣ ባርካ ቡሊማ እና ጆን ፓምባ ናቸው ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ ኬንያ የገቡት የሟች አባትን ጨምሮ፣ እናቱና እና በርካታ የቤተሰቡ አባለት ፍርድ ቤት ብይን በሰጠበት ጊዜ ነበር።