በሀገር ውስጥ የተገጣጣሙ ሞተር ሳይክሎችን እያመረተች የምትገኘው ሩዋንዳ

የሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ከበርካታ የአፍሪካ አገራት በተቃራኒ የአገሬውም ይሁን የውጪ ዜጋ በቀን እና በማታ ያለምንም የደኅንነት ስጋት የሚንቀሳቀሱባት ከተማ ስለመሆኗ ብዙዎች ይመሰክሩላታል።

ማራኪ በሆኑ መስህቦች የተሞላችው ኪጋሊ ንጽህናዋ በዓለም ካሉ ጽዱ ከተሞች ጋር የሚያወዳድራት ነው። ከ850 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ያሏት ኪጋሊ መገለጫ ጽዳቷና ደኅንንቷ ብቻ አይደለም።

ያለፋታ ውር ውር የሚሉት ሞተር ሳይክሎች የተማዋ እንቅስቃሴ የደም ስር እና ድምቀት ናቸው።

ከተማዋ ካላት የትራንስፖርት አማራጮች ሞተር ሳይክል እጅግ ከተለመዱት ውስጥ ነው። በተለምዶ 'ሞቶስ' የሚባሉት ሞተር ሳይክሎች ለበርካቶች የገቢ ምንጭ ናቸው።

ከእነዚህ አንዱ የሆነው ዲዲየር ናዳባያህሪ በጽዱዎቹ የኪጋሊ ጎዳናዎች ከ12 ዓመታት በላይ መንገዶኞች እያመላለሰ ኑሮውን እየገፋ ነው።

በነዚህ ዓመታት ለሞተር ሳይክሉ ነዳጅ እየቀለበ ሲሰራ ቆይቷል። በቅርቡ ግን በኤሌክትሪክ የሚሰራ ሞተር ሳይክል ማሽከርከር ጀምሯል። ለዲዲየር የመጀመሪያዎቹ ጊዜዎች ፈታኝ ቢሆኑም አሁን ለነዳጅ የሚያወጣውን ገንዘብ እንዲቆጥብ ረድቶታል።

"በመጀመሪያዎቹ ቀናት ነገሮች ጥሩ አልነበሩም። ምክንያቱም በኤሌክትሪክ የሚሰራ ሞተር ሳይክል ነድቼ ስለማላውቅ እና አንዳንድ ጊዜ ስለሚቋርጥ ነው። ነገር ግን መስራቴ ቀጠልኩ እና ብዙም ሳልቆይ ብስክሌቱ እንዴት እንደሚሰራ እና እንዴት መንዳት እንዳለብኝ ብዙ ነገሮችን ተረዳሁ። ከዚያም ብዙ ገንዘብ መቆጠብ ቻልኩ " ሲል ዲዲየር ያስረዳል።

አሽከርካሪው በሩዋንዳው 'አምፐርሳንድ' ከተሰኘ ኩባንያ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ሞተር ካገኙ 60 አሽከርካሪዎች አንዱ ነው።

እናም አዲሱ ሞተር ለዲዲየር የተስማማ ሆኗል። "አሁን ሞተሩን ወድጄዋለሁ። በነዳጅ ከሚሰሩት ሞተሮች በተለየ ምንም አይነት ችግር ሳይኖር ለረጅም ጊዜ በጥሩ ሁኔታ መነዳት ይችላል። ሲነዳም በጣም ምቾት አለው" ብሏል።

በዚህ የሥራ ዘርፍ የተሰማራው 'አምፐርሳንድ' በኤሌክትሪ የሚሰራ ሞተር ሳይክል በማምረት በአፍሪካ ጭምር ፈር ቀዳጅ ከሆኑት መካከል ሲሆን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሩዋንዳ ሞተር ሳይክሎችን ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ ለመቀየር ተስፋ አድርጓል።

ይህ የኩባንያው ትልም ነው። በኪጋሊ ወደ 25 ሺህ የሚጠጉ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ሞተር ሳይክሎች ያሉ ሲሆን በቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ይሸፍናሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ በቀን እስከ 10 ሰዓታት ያሽከረክራሉ።

"በዓለም ካሉት ተሽከርካሪዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን የሚሸፍኑት ሞተር ሳይክሎች ናቸው" የሚሉት የአምፐርሳንድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጆሽ ዌል "ቀላሎቹ ሞተሮች በዘመናዊ መኪኖች ወይም በሞተር ሳይክሎች ውስጥ የአየር ብክለት መቀነሻ ቴክኖሎጂ የላቸውም። ይህም ሆኖ እነዚህ ሞተሮች በቀን ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ እየሸፈኑ ነው። ያ ደግሞ ብዙ ብክለት ነው" ሲል ገልጸዋል።

"በሩዋንዳ አሽከርካሪዎች በአንድ ዓመት ውስጥ ለነዳጅ የሚያወጡት አዲስ ሞተር ሳይክል መግዛት ይችላል። አሁን ጥቅም ላይ ከዋሉ ሞተር ሳይክሎች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ እና ዝቅተኛ የክትትል ወጪን የሚጠይቁ አማራጭ ማቅረብ እንደምንችል አሳይተናል" ሲሉ አክለዋል።

እናም እንደ ኩባንያው እምነት የነዳጅ ወጪን ማስቀረት እና የጥገና ወጪን መቀነስ የአሽከርካሪዎቹን ገቢ በእጥፍ ይጨምረዋል።

በምሥራቅ አፍሪካ ጎዳናዎች ላይ አምስት ሚሊዮን የሚገመቱ ሞተር ሳይክሎች እንዳሉ ይገመታል። ታዲያ 'አምፐርሳንድ' እና መሰል ኩባንያዎች በገበያው ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ማሳደግ ከቻሉ የበካይ ጋዝ መጠንን ትርጉም ባለው ደረጃ ይቀንሱታል።

ይህ የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክል የሚሰራው ሩዋንዳዊ ኩባንያ ሞተር ሳይክሎች እና ባትሪዎችን ከመገጣጠም በተጨማሪ ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን ዘርግቷል።

በኪጋሊ የሚገጣጠሙት የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክሎች ከ150 የአካል የሞተር ሳይክል ክፍሎች የተዋቀሩ ሲሆን ባትሪዎቹ በተለየ ትኩረት ንዳፍቸው በአምፐርሳንድ መሐንዲሶች ይሰራሉ። ከዚያም ውጪ አገር ተመርተው ወደ ሩዋንዳ ተልከው በአገር ውስጥ ቴክኒሻኖች ይገጣጠማሉ።

ይህ ኩባንያ በስሩ 73 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ምርቱ እያደገ በመምጣቱ የመገጣጠሚያ ቦታውን እየቀየረ ይገኛል። ከታላላቅ የሞተር ሳይክል አምራቾች ጋር የመስራት ፍላጎትም አላቸው።

"አሁንም ትንሽ አነስተኛ ኩባንያ ነን። በአየር ንብረት ቀውሱ ፍጥነት መቀየር እንፈልጋለን። ስለዚህ አንዳንድ ከባድ የሚባሉ ነገሮችን በፍጥነት መስራት እንችላለን። በምንችልበት ቦታ ከትላልቅ እና ነባር ተቋማት ጋር ተባብረን ብንሰራ በጣም ደስ ይለናል" በማለት ዌል ገልጸዋል።

ኩባንያው ቻርጃቸው የተሟጠጡ ባትሪዎችን ቻርጅ በተደረጉ የሚቀይርባቸን የነዳጅ ማደያ ሥራን አይነት አገልግሎት የሚሰጡ አምስት ጣቢያዎች በኪጋሊ ክፍት አድርጓል።

እያንዳንዱ የቻርጅ ጣቢያ ለመገንባት 5 ሺህ ዶላር እንደሚፈጅ የሚገልጸው ኩባንያው አንድ የነዳጅ ማደያ ለመገንባት የሚወጣ ዋጋ ወደ 20 የሚጠጉ የቻርጅ ጣቢያዎችን መገንባት እንደሚችል ጠቁሟል።

የሩዋንዳ መንግሥት በአገሪቱ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለማበርከት ወይም ወደ ኢ-ትራንስፖርት ለመሸጋገር ትልቅ ሥራ እየሰራ ይገኛል።

የዚህ ዘርፍ መስፋፋት ከነዳጅ ታክስ የሚገኝ ገቢን እንደሚቀንሰው ቢታመንም የተሽከርካሪዎችን የኃይል ምንጭ ወደ አገር ውስጥ መቀየር፣ ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ የሚገባበትን ወጪን መቀነስ እና በአገር ውስጥ ሲገጣጠሙ ደግሞ የሥራ ዕድል መፍጠርን የመሳሰሉ ጥቅሞችን ያስገኛል።

በሩዋንዳ ቮልስዋገን እንደ አውሮፓውያኑ ከ2019 ጀምሮ ከሲመንስ ጋር በመተባበር የኤሌክትሪክ ተሽክርካሪዎችን የሙከራ ፕሮጀክት ሲያካሂድ ቆይቷል። እስካሁንም ሁለት ቻርጅ ማድርጊያ ጣቢያዎች ገነባ ሲሆን 20 መኪኖችንም አምርቷል።

የቮልስዋገን ኩባንያ አገሪቱ በነዳጅ ከሚሰሩ ሞተሮችን ወደ ኤሌክትሪክ መኪኖች የመሸጋገር አቅም እንዳላት ተናግሯል።

በሞተር ሳይክሎች ላይ የተሰማራው አምፐርሳንድ ደግሞ በአፍሪካ ላለው ትልም ሩዋንዳ መነሻው ስትሆን፣ ኩባንያው በአሁኑ ጊዜ በኬንያ እና በሌሎች አገራት ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሥራውን ይጀምራል።

በአፍሪካ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለማምረት ችግር የሚሆኑ ነገሮች እንዳሉ ቢጠቀስም የሩዋንዳው ሞተር ሳይክል ገጣጣሚ ኩባንያ ባለቤት ግን አህጉሪቱ በዘርፉ ቀዳሚ መሆን እንደምትችል ያምናል።

የሚፈለገው የሥራ ካፒታል መጠን ደግሞ "በቀላሉ ሊገኝ የሚችል" ነውም ብሏል።

ጨምሮም "የኤሌክትሪክ ዘመን እዚህ እንዳለ ማሳየት እንደምንችል ተስፋ እናደርጋለን። ከአየር ብክለት የጻዳ መጓጓዣ ለአሥርት ዓመታት ካገለገለ በኋላ ወደ ታዳጊ አገራት የሚላክ አይደለም። ይልቁንም አሁን ኢንቨስት የሚደረግበት ወጪ ቆጣቢ እና ለኢንቨስትመንት የሚመች ነው" ሲል ገልጿል።