ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በቅርቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ተነገረ

ሕዳሴ

የፎቶው ባለመብት, @seleshi_b_a

ኢትዮጵያ በቅርቡ ከግዙፉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደምትጀምር ተገለጸ።

አንድ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣንን ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ግድቡ በመጀመሪያ ደረጃው የኃይል ማመንጨት ሥራው 700 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሏል።

ይህም አገሪቱ እያመነጨች ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል በ14 በመቶ ከፍ እንደሚያደርገው ተነግሯል።

የኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት ሁሪያ አሊ የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ፌስቲቫል ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የተለያዩ የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶችን እያካሄደች መሆኑ አመለክተዋል።

ከእነዚህ ውስጥም ሊጀመር ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ በቀረው ቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት "700 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚጀምረው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አንዱ ነው" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የቀድሞው የውሃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትሩ እና የአሁኑ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና የህዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪና አማካሪ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የሕዳሴ ግድቡ በ2014 ዓ.ም. መጀመሪያ ወራቶች ላይ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀመር ከወራት በፊት ተናግረው ነበር።

ኢትዮጵያ ለአስር ዓመታት እየገነባችው ባለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር መቋጫ ላይ ያልደረሰ ጠንካራ ድርድር ስታደርግ የቆየች ሲሆን ግብጽ እና ሱዳን በግድቡ ውሃ አሞላል እና ኦፕሬሽን ላይ ከስምምነት ሳይደረስ የግድቡ ውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ ሲወተውቱ ቢቆይም አሁን ግድቡ ኃይል ወደ ማመንጨቱ ተቃርቧል።

ግብፅና ሱዳን ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ እየገነባችው ያለው ግዙፍ ግድብ ከአባይ ወንዝ የሚያገኙትን ውሃ ሊቀንስብን ይችላል በሚል ስጋታቸውን አስከ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አቅርበው ነበር።

ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ግድብ ዋነኛ ዓላማው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በመሆኑ በግብፅና በሱዳን ላይ ጫና ከመፍጠር ይልቅ የሚያጋጥማቸውን የደለልና የጎርፍ አደጋዎች በመቀነስ የተመጣጠነ ውሃ እንዲያገኙ ያደርጋል ስትል ስትከራከር ቆይታለች።

ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ በግዝፈቱ እና በሚያመነጨው ኃይል በአፍሪካ አህጉር ቀዳሚው የሚሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፤ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክተሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የኃይል ማመንጫ ግድቦቿ 4,967 ሜጋ ዋት የኤሌከትሪክ ኃይል የምታመነጭ ሲሆን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የኃይል ማመንጨት አቅሟን በእጥፍ ያሳድገዋል።

የግድቡን የኃይል ማመንጨት የሚጠባበቁት የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችን የዘረጉ ሲሆን የኃይል ሽያጭ ስምምነቶችንም እያደረጉ ነው።