ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአየር ላይ የሚበርሩ ታክሲዎችን መጠቀም የምንጀምረው መቼ ይሆን?
ለበርካታ ሰዎች በአየር ላይ የሚበርሩ ታክሲዎች ነገር በፊልሞች ላይ ብቻ የሚታይ መስሎ ሊታሰብ ይችላል።
ነገር ግን እንደ ኡበር እና ቦይንግ ያሉ ድርጅቶች በኤሌክትሪክ የሚሰሩና በደቂቃዎች ውስጥ በአየር ላይ ከተፍ ብለው ትራፊክ ተጨናነቀ መንገድ ተዘጋ ሳይሉ ያሰቡበት ቦታ ለማድረስ እየሰሩ ነው።
እንደውም በአውሮፓውያኑ 2040 በመላው ዓለም ይህን መሰል አገልግሎት የሚሰጡ 430 ሺ በራሪ ታክሲዎች እንደሚኖሩ ይገመታል።
ይህ የመሆን እድሉ ከፍተኛ የሚያደርገው ደግሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በራሪ መኪናዎችን በመሞከር ላይ መሆናቸው ነው። አንድ ጥናት እንደሚያመላክተው ይህ ዘርፍ በአውሮፓውያኑ 2028 እስከ 5.6 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ የማንቀሳቀስ አቅም አለው።
ይህንን የመሰለ የወደፊት ገበያን ለመቆጣጠር ደግሞ በአሁኑ ሰአት የተጀመሩት በራሪ ታክሲዎች እና ድሮኖች ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል። እንደውም በቅርብ ዓመታት ውስጥ የሚበርሩ መኪናዎች የሚበዙ ከሆነ ትልልቅ ከተሞች 'ስካይፖርትስ' የተሰኙ የአየር ላይ ኤርፖርቶች መገንባት ግዴታቸው ይሆናል ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።
እነዚህ አነስተኛ የአየር ላይ ኤርፖርቶች ታክሲዎቹ የሚያመላልሷቸውን ደንበⶉች ለመጫን እና ለማውረድ ይጠቀሙባቸዋል ማለት ነው።
መቀመጫውን አሜሪካ ካሊፎርኒያ ያደረገው ጆቢ ኤቪዬሽን በአሁኑ ሰአት በራሪ መኪናዎችን በማምረት ቀዳሚ የሚባል ድርጅት ነው። እስካሁንም የበራሪ መኪናዎቹን ደህንነትና ውጤታማነት የሚፈትሹ ከ1 ሺ ጊዜ በላይ የሙከራ በረራዎችን አድርጓል።
ድርጅቱ በቅርቡም ከአሜሪካ የፌደራል ኤቪዬሽን አስተዳደር ፈቃድ እንደሚያገኝ ተስፋ ሰንቋል። በአውሮፓውያኑ 2024 ደግሞ በራሪ መኪናዎቹን ጥቅም ላይ ለማዋል አቅዶ እየሰራ ነው የሚገኘው።
የጆቢ በራሪ መኪናዎች ለጊዜው እስከ አራት ሰዎችን መያዝ እንዲችሉ ተደርገው ሲሆን የተሰሩት በሰአትም እስከ 322 ኪሎ ሜትር ድረስ የመምዘግዘግ አቅም አላቸው ተብሏል።
''በራሪ ታክሲዎቻችን ሰዎች በጋራ ሊጠቀሟቸው የሚችሉና ከመኖሪያቸው አልያም ከስራ አካባቢያቸው እንዲነሱ የሚደረጉ ናቸው'' ይላሉ የጆቢ ቃል አቀባዩ ኦሊቨር ዎከር ጆንስ።
'' የእኛ በራሪ መኪናዎች ከሌሎች የትራንስፖርት አማራጮች ጋር የተስማሙ እንዲሆኑ በማሰብ ከወዲሁ ከከተማ አስተዳደሮች ጋር በቅርበት እየሰራን ነው። አነስተኛ የአየር ላይ ኤርፖርቶቻችንም ከባቡር ጣቢያዎች፣ አየር ማረፊያዎችና ሌሎች ማዕከላት ጋር በጥምረት እንዲሰሩ ነው የምንፈልገው።''
ከዚህ በተጨማሪም ጆቢ የፓርኪንግ አገልግሎት ከሚሰጠው የአሜሪካው ሪፍ ቴክኖሎጂ ጋር በጥምረት መስራት የጀመረ ሲሆን፣ ድርጅቱ ለመኪና ማቆሚያ የሚጠቀምባቸውን ህንጻዎች ጣሪያ ወደ ጆቢ ማዕከልነት ለመቀየር እየሰራ ነው። በተጨማሪም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በተመሳሳይ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ ነው።
''ከእነዚህ አጋሮቻችን ጋር በመሆን ስካይፖርትስ ለመገንባትና በቀላሉ ለደንበኞቻችን አገልግሎት ለመስጠት ነው እቅዳችን። በመንገዶች ላይ የሚኖረውን መጨናነቅ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ይቻላል።"
ምንም እንኳን ድርጅቱ በሚያስበው ልክ በርካታ የአየር ላይ አነስተኛ ኤርፖርቶችን መገንባት የማይታሰብ ነገር ሊመስል ቢችልም ጥቂት የማይባሉ የአሜሪካ ከተሞችና ግዛቶች ይህንን ነገር ለመሞከር ፈቃደኝነታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ከነዚህም መካከል ሂውስተን፣ ሎስ አንጀለስ እና ኦርላንዶ ለበራሪ ታክሲዎች ማረፊያና መነሻ የሚሆኑ መሰረት ልማቶችን ከወዲሁ ለማስገንባት በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የሎስ አንጀለሱ ከንቲባ ኤሪክ ጋርሴቲ እንደሚሉት ለከተማዋ የቀረበው እቅድ ሌሎች የከተማ አሰረተዳደሮችም ወደፊት በምን አይነት መንገድ መጓዝ እንዳለባቸው ማሳያ ነው።