ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቴክኖሎጂ ፡ ከተኙ በኋላ ስልክዎን ሳይንቲስቶች እንዲጠቀሙበት ይፈቅዳሉ?
ሀና ላውሰን-ዌስት የምትኖረው ለንደን ነው።
ዘወትር ከመተኛቷ በፊት ፊቷን ትታጠባለች፣ ጥርሷን ትቦርሻለች። ከዚያም ስልኳ ላይ ዜና ትመለከታለች፣ የኢንስታግራም ገጿን ትጎበኛለች።
መጨረሻ ላይ ስልኳ ቻርጅ እንዲያደርግ ሰክታ ትተኛለች።
የ31 ዓመቷ ሀና ለስምንት ሰዓታት ስትተኛ ስልኳ ግን ይነቃል። ሳይንቲስቶች ባሉበት ሆነውም ይጠቀሙበታል።
ሀና ስልኳ ከአጠገቧ ሳይርቅ ኮሮናቫይረስ ላይ ምርምር የሚሠሩ ሰዎች እንዲጠቀሙበት የሚያስችል አሠራር ተከታይ ናት።
የዚህ አሠራር ተከታይ ከሆነች ዓመት ተቆጥሯል። ሳይንቲስቶች ስልኳን ተጠቅመው እስካሁን 2,500 የኮምፒውተር ስሌት ሠርተዋል።
የዚህ አሠራር አመንጪ ‘ድሪምላብ’ መተግበሪያ ነው። ሰዎች ከተኙ በኋላ ሳይንቲስቶች ስልካቸውን የሚጠቀሙበት መንገድ ዘርግቷል።
በመላው ዓለም 100,000 ሰዎች ስልካቸውን በፈቃደኝነት ለአገልግሎቱ ሰጥተዋል።
መተግበሪያው ያተኮረው የኮሮናቫይረስ መድኃኒት ላይ ነው።
ሰዎች ምን አይነት ንጥረ ነገር ያለው ምግብ ቢመገቡ ለኮቪድ-19 ሕክምና አጋዥ ይሆናል? የሚለው ላይ ጥናት እየሠሩ ነው። ጥናቱ በተለይም በሽታው ዘለግ ላለ ጊዜ የሚቆይባቸው ሰዎች ላይ ያተኩራል።
ምግብ ከበሽታው ስለመከላከሉ ወይም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መመገብ ስላለባቸው ነገር እስካሁን ተጨባጭ መረጃ አልተገኘም።
እየተሠራ ያለውን ጥናት የሚመሩት የለንደኑ ኢምፔሪያል ኮሌጅ እና ቮዳፎን ፋውንዴሽን ናቸው።
‘ድሪምላብ’ ከተባለው መተግበሪያ በተጨማሪ ‘ኢቭኦንላየን’ እና ሌሎችም መተግበሪያዎች ለኮቪድ-19 ምርምር በጎ ፈቃደኞችን ያሰባስባሉ።
ለሳይንቲስቶች ስልክ ‘ማዋስ’
ሂደቱ ‘ቮሉንተር ኮምፒውቲንግ’ ይባላል።
የስልኮች አቅም አንድ ላይ ሲሰባሰብ የተከማቸ መረጃን በሦስት ወር ማስላት ይቻላል። ይህ ሥራ ለአንድ መደበኛ ኮምፒውተር 300 ቀን ይወስድበታል።
ሀና መተግበሪያውን የጫነችው አባቷ የደም ካንሰር ሲገኝባቸው ነበር።
መጀመሪያ የተሳተፈችበት ፕሮጀክት የካንሰር መድኃኒት ላይ ያተኮረ ነው። አሁን ደግሞ በኮቪድ-19 ፕሮጀክት ላይ ትሳተፋለች።
“ተኝቼ ውጤታማ ነገር ማድረጌ ሁሌም ይደንቀኛል። ብዙ ሰዎች መሳተፍ አለባቸው” ትላለች።
እንደ ሀና ባሉ በጎ ፍቃደኞች አማካይነት 53 ሚሊዮን ስሌቶች ማከናወን ተችሏል።
ዓለም አቀፉ መተግበሪያ በደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ ፖርቹጋል፣ ዩናይትድ ኪንግደምና ሌሎችም አገሮች ተጠቃሚዎች አሉት።
ሌላዋ በጎ ፍቃደኛ አንጅሊካ አዝቬዶ የምትሮረው ሊዝበን ነው።
“እናቴ በወረርሽኙ ወቅት በደም ካንሰር ሳቢያ ነው የሞተችው። ከሕክምና ጋር የተያያዙ ጥናቶችን ለመደገፍ የወሰንኩትም ለዚህ ነው። ለኮቪድ-19 መድኃኒት እንዲገኝ እንደማግዝ አምናለሁ” ትላለች።
የ28 ዓመቷ አንጅሊካ ዘወትር ከእንቅልፏ ስትነሳ መጀመሪያ የምታደርገው ነበር መተግበሪያውን መመልከት ነው።
እሷ ተኝታ ሳለ በስልኳ ምን ያህል የኮምፒውተር ስሌት እንደተሠራ ማየት ቀኗን ብሩህ እንደሚያደርገው ትናገራለች።
ሳይንቲስቶች ምን ይላሉ?
ፕ/ር ኪሪል ቨልስኮቭ የበጎ ፍቃደኖች ድጋፍ ኮቪድ-19 ላይ የሚደረገውን ምርምር እንዳፋጠነ ያስረዳሉ።
“100,000 ተንቀሳቃሽ ስልኮች ከፈጣን ኮምፒውተሮች ሁለትና ሦስት እጥፍ የተሻሉ ናቸው” ይላሉ።
በእያንዳንዱ ስልክ ላይ የሚሠሩት ስሌት የትኛው ንጥረ ነገር ያለው ምግብ ለኮሮናቫይረስ ታማሚ እንደሚረዳ ይፈትሻል።
ጥናቱ ከ50 በላይ ሞለኪውሎች ኮቪድ-19ኝን የመከላከል አቅም እንዳላቸው የሚጠቁም ግኝት ላይ ደርሷል።
ዶ/ር ሳይመን ክላርክ ተንቀሳቃሽ ስልክን በመጠቀም አጥኚዎች ምርምር ማካሄድ መቻላቸው ያስደንቃቸዋል።
የበጎ ፍቃደኖችን ስልክ ሳይንቲስቶች የሚጠቀሙበት ሂደት እአአ በ1990ዎቹ ነው የተጀመረው።
ሲጀመር ከ100,000 በላይ በጎ ፍቃደኞች ነበሩት።
ያኔ የተካሄደው ምርምር ከምድር ውጪ ሕይወት ያላቸው አካሎች ይኖሩ እንደሆነ የሚፈትሽ ነበር።
ከጥናቱ መስራቾች አንዱ ዶ/ር ዴቪድ አንደርሰን ፕሮጀክታቸውን ሌሎችም ሳይንቲስቶች እንዲጠቀሙበት ክፍት አድርገዋል።
“አብዛኛው የኮምፒውተር ስሌት ያለው በፈጣን ኮምፒውተር ማዕከሎች ወይም በክላውድ ሳይሆን በሰዎች ቤት ነው” ይላሉ ተመራማሪው።
ዴስክቶፕ፣ ስልክ፣ መኪናና ሌሎችም ቁሳቁሶች ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ያስረዳሉ።
“በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ስልኮች፣ ዴስክቶፖች ወዘተ አሉ። እነዚህ ሳይንሳዊ ምርምርን ያፋጥናሉ” የሚሉት ዶ/ር ሳይመን በጎ ፍቃደኞችን ያመሰግናሉ።