ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዝዳንት ባይደን ቻይና ታይዋን ላይ ጥቃት ብትሰነዝር አሜሪካ ታይዋንን ተከላከላለች አሉ
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ቻይና ታይዋንን ብታጠቃ አሜሪካ ከታይዋን ጎን ቆማ ትከላከላለች ሲሉ ተናገሩ።
ይህ የባይደን ንግግር አሜሪካ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ለውጥ ማሳየቷን ያመላከተ ነው ተብሏል።
ከባይደን ንግግር በኋላ ግን የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ የባይደን ንግግር ታይዋንን በተመለከተ የአሜሪካ መንግሥት የፖሊሲ ለውጥ ማድረጉን አያሳይም ብለዋል።
አሜሪካ ታይዋን እራሷን እንድትከላከል እንድትረዳ የሚያስገድድ ሕግ አላት። ይህ ሕግ ግን ሆነ ተብሎ ግልጽ እንዳይሆን ተደርጓል።
በዚህም ቻይና ታይዋንን ብታጠቃ የአሜሪካ ምላሽ በትክክል ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ አይደለም።
የባይደንን አስተያየት ተከትሎ እስካሁን ቻይና ያለችው ነገር የለም።
ባይደን እና ዋይት ሐውስ ምን አሉ?
ሲኤንኤን ባዘጋጀው ውይይት ላይ አንድ ተሳታፊ ቻይና በቅርቡ ያደረገችውን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ሙከራ በማስታወስ፤ ቻይና ታይዋንን ብታጠቃ ባይደን ታይዋንን ለመጠበቅ ቁርጠኝ ስለመሆናቸው ጠይቆ ነበር።
ባይደንም ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ "አዎ" ብለዋል። "የበለጠ ኃይል ያላቸው አገራት እየሆኑ ቢሄዱ ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም።" ምክንያቱም "ቻይና፣ ሩሲያ እና መላው ዓለም እኛ በዓለም ታሪክ ውስጥ የበለጠ ወታደራዊ ኃይል እንዳለን ያውቃሉ" ሲሉ ባይደን ተናግረዋል።
ቀጥሎ የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ታይዋን በቻይና ጥቃት ቢፈጸምባት አሜሪካ ታይዋንን ትከላከላለች ወይ? ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ፤ ባይደን "አዎ፤ ያን የማድረግ ግዴት አለብን" ብለዋል።
ከባይደን ንግግር በኋላ የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ የባይደን ንግግር ምንም የተለወጣ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሰለመኖሩ አያመለክትም ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የታይዋን ፕሬዝደንት ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ፈጥኖ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
"ታይዋን እራሷን ለመከለከል ቆራጥነትን ታሳያለች" ሲሉ የፕሬዝደንቱ ቃል አቀባይ ቫቪዬር ቼንግ ተናግረዋል።
ቻይና እስካሁን የባይደን ንግግርን ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ያለችው ነገር ባይኖርም ሐሙስ ዕለት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቻይና አምባሳደር የሆኑት ዛንግ ጁን "አሜሪካ በታይዋን ጉዳይ አደገኛ አቅጣጫን መርጣለች" ሲሉ የባይደን አስተዳደርን ተችተዋል።
ባለፉት ሳምንታት ቤጂንግ ተዋጊ አውሮፕላኖቿን በታይዋን የአየር ክልል ላይ ማብረሯን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት ነግሶ ቆይቷል።
የቻይና እና ታይዋን ግንኙነት ለምን የሻከረ ሆነ?
ቻይና እና ታይዋን የተለያዩት እእአ 1940ዎቹ በነበረው የእስር በእስር ጦርነት ወቅት ነው። ከዚያ በኋላ ታይዋን እራሷን እንደ ነጻ ሉዓላዊት አገር ትመለከታለች። ቻይና ግን እንደ አንድ ተገንጥለ እንደወጣች ግዛቷ ትቆጥራታለች።
ቻይና ታይዋን ወደፊት አስፈላጊም ከሆነ በኃይል የቻይና አንድ አካል ሆነ ትቀጥላለች የሚል አቋም አላት።
ታይዋን የምትተዳደረው እንዴት ነው?
ታይዋን የምትመራበት የራሷ የሆነ ሕገ-መንግሥት አላት። በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጡ መሪዎች አሏት። ከ300 ሺህ ያላነሰ የጦር ሠራዊት አባላትም አላት።
ለታይዋን ማን እውቅና ይሰጣል?
ታይዋንን እንደ አገር እውቅና የሚሰጡት ጥቂት አገራት ከመሆናቸውም በተጨማሪ በተጽእኖ ፈጣሪነታቸው እዚህ ግባ የማይባሉ አገራት ናቸው። ለታይዋን እውቅና ከሚሰጡ አገራት መካከል ጓቲማላ፣ ሆንዱራስ፣ ኢስቲዋኒ እና ኒኳሯጋ ይገኙበታል።
ለታይዋን ጠንካራ አጋርነቷን የምታሳየው አሜሪካም ብትሆነ ከታይዋን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የላትም። የጦር መሳሪያዎችን ግን ለታይዋን ትሸጣለች።
አሜሪካ ለታይዋን የጦር መሳሪያ የምትሸጠው ታይዋን እራሷን እንድትከላከለ የመርዳት ኃላፊነት ስላለብኝ ነው ትላለች።