የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆም ዳግም ጠየቀ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በሚካሄደው ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ግጭት እንዲያቆሙ ዳግም ጠየቀ።

ከተመድ በተጨማሪ ምዕራባውያን አገራት እና የረድኤት ድርጅቶች ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ጦርነቱ በውይይት እንዲፈታ እና የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ሲወተውቱ ቆይተዋል።

"በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ተጨማሪ ጉዳቶችን እና በሲቪሎች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ለማስቀረት የግጭቱ ተሳታፊ አካላት ከግጭት እንዲቆጠቡ ጥሪያችንን ደግመን እናሰማለን" ብለዋል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ቃል አቀባይ ፋረሃን ሃቅ።

"በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ሕጎችን ማክበር አለባቸው፤ ንፁሑሃን ዜጎችን እና መሠረተ ልማቶችን መጠበቅ አለባቸው" ብለዋል።

የተመድ ቃል አቀባይ ይህን ያሉት፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚደረገው ጦርነት ተጠናክሮ በቀጠለበት እና የፌደራሉ ኃይል በትግራይ መዲና መቀለ ተደጋጋሚ አየር ድብደባ እያደረገ ባለበት ወቅት ነው።

ምክትል ቃል አቀባዩ ጦርነቱ በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ከተስፋፋ በኋላ፤ በአፋር እና አማራ ክልሎች የሰብዓዊ እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው ብለዋል።

የፌደራሉ መንግሥት ተቆጣጥሮት ከነበረው ትግራይ ክልል የተናጠል የተኩስ አቁም ውሰኔ አውጆ ከትግራይ አካባቢዎች መውጣቱን ተከትሎ፤ አማጺያኑ በመልሶ ማጥቃት በርካታ የትግራይ ስፍራዎችን ከመቆጣጠር አልፈው በጎረቤት ክልሎች ላይ ወረራ መፈጸማቸው ይታወሳል።

በዚህም የትግራይ ኃይሎች የሰሜን እና ደቡብ ወሎ አካባቢዎችን ይዘው ይገኛሉ።

የትግራይ ኃይሎችን እየመሩ ካሉት መካከል አንዱ የሆኑት ጀነራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ፣ በአፋር እና አማራ ክልሎች ጥቃት የከፈቱት በፌደራሉ መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ጄነራል ጻድቃን ከጦር ኦፕሬሽኖቻቸው ዓላማዎች አንዱ የፌደራሉ መንግሥት የትግራይ ኃይሎች የተኩስ አቁም ለማድረግ ያስቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች ተቀብሎ ወደ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲመጣ ለማስገደድ መሆኑን ከቢቢሲ 'ኒውስ አወር' ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅእ ነበር የተናገሩት።

የአማጺያኑን ጥቃት ተከትሎ ከሰሜን እና ደቡብ ወሎ እንዲሁም ዋግ ኅምራ እንዲሁም ከአፋር አካባቢዎች በርካቶች ተፈናቅለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ከአማራ እና አፋር ክልል አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወደ 1.7 ሚሊዮን ሕዝብ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ነበር።

የተመድ ምክትል ቃል አቀባይ ፋረሃን ሃቅ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ የግጭቱን መስፋፋት ተከትሎ በአማራ እና አፋራር የሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን አስታወሰዋል።