የታጠፉ፣ እንደ አዲስ የተዋቀሩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና የካቢኔ ሹም ሽር በዓመታት

ስድስተኛውን ዙር ምርጫ ተከትሎ በነገው ዕለት አዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ይመሠረታል። በተመሳሳይ ባለፉት ዓመታት በተለያየ ጊዜያት የመንግሥት ምሥረታዎች ተከናውነዋል።

አዲስ አስተዳደር ሲመሠረት በሥራ አስፈጻሚው ላይ ለውጦች ተደርገዋል። በዚህም በርካታ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ታጥፈዋል፣ አዲሶች ደግሞ ተቋቁመዋል። ባለስልጣናትም በፍጥነት ከቦታ ወደ ቦታ ተቀያይረዋል።

ወርሃ ጥቅምት 1994 የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከነበሯቸው 15 የካቢኔ ሚኒስትሮች 10ሩን የቀየሩበት ነበር።

በወቅቱ የመሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር እና የገጠር ልማት ሚኒስቴር ቀደም ሲል ያልነበሩ አዳዲስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሆነው ብቅ ብለዋል።

ቦታቸውን ካስጠበቁት ሚንስትሮች መካከል የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን እና የትምህርት ሚኒስትሯ ገነት ዘውዴ (በወቅቱ ብቸኛዋ የሴት ሚኒስትር) ይገኙበታል።

የወ/ሮ ገነት ዘውዴ ባለቤት ዶ/ር ከበደ ታደሰ የጤና ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ ጥንዶቹ ሚኒስትሮች ለመሆን በቅተዋል።

አቶ አባዱላ ገመዳ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ አቶ አዲሱ ለገሰ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የገጠር ልማት ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። በዚህ ወቅት ነበር አቶ በረከት ስምኦን የማስታወቂያ ሚኒስትር የሆኑት።

ከአይረሴው ምርጫ 97 በኋላ ጥቅምት 03/1998 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቅርብ ሰዎቻቸውን እና ረዥም ጊዜ ያገለገሉ ሚኒስትሮችን የተኩበት ነበር።

ቀደም ሲል 17 የነበረው የካቢኔያቸውን ቁጥርም ወደ 20 አሳድገዋል።

ገነት ዘውዴ፣ ባለቤታቸው ከበደ ታደሰ እና በረከት ስምኦን ከሚኒስትርነታቸው የተነሱበትም ነበር። አዲሱ ለገሰ እና ስዩም መስፍን ደግሞ ቦታቸውን አስጠብቀዋል።

መስከረም 24/2001 ዓ.ም የካቢኔ ሽግሽግ ተደረገ።

ኋላ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሚኒስትር ማዕረግ የፓርላማው የመንግሥት ተጠሪ ሆኑ። ሲራጅ ፈርጌሳ የመከላከያ ሚኒስትር ሲሆኑ አቶ ደመቀ መኮንን ደግሞ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ። ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የሴቶች ጉዳይን እንዲመሩ ኃላፊነት ተሰጣቸው።

በዚሁ ወቅትም የኢትዮጵያ ራዲዮ እና ቴሌቭዥንን ጨምሮ መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃንን በበላይነት የሚመራው የማስታወቂያ ሚኒስቴር እንዲፈርስ ተደረገ።

ኢሕአዲግ በ2002 ምርጫ ካሉት 547 የፓርላማ ወንበሮች 545 አሸንፎ መስከረም 25/2003 ዓ.ም መለስ ዜናዊን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾመ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔያቸውን ሲያሳውቁ ለ19 ዓመታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉትን ስዩም መስፍንን በኃይለማርያም ደሳለኝ ተክተዋል። ኃይለማርያም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርም ነበሩ።

የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትሩ ግርማ ብሩ እና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አዲሱ ለገሰ ከኃላፊነታቸው ተነሱ። ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል የኮምዩኒኬሽን እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆኑ።

የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለሁለት ተከፍሎ የማዕድን ሚኒስቴር እና የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሆን ተወሰነ።

ኅዳር 20/2005

የመለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወትን ተከትሎ ወደ መንበሩ የመጡት ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን ከተረከቡ ከአንድ ወር በኋላ የካቢኔ ሽግሽግ በማድረግ ሥራ ጀመሩ።

ተጨማሪ ሁለት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና አዲስ የውጭ ጉዳይ እና የንግድ ሚኒስትር አስተዋወቁ።

የኮምዩኒኬሽን እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል እና አዲስ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ሆነው ተሹመው የነበሩት ሙክታር ከድር ናቸው ነባሩን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን በመቀላቀል ሦስቱን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታዎች የያዙት።

አቶ ሙክታር ከድር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ክላስተር አስተባባሪ እንዲሁም ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

አገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሮች የተሾመላት።

በዚሁ ወቅት ነበር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የሆኑት። ዶ/ር ቴድሮስ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ ደግሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ተኳቸው።

ከወራት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አቶ በረከት ስምኦንን የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር አማካሪያቸው አድርገው ሾሙ።

መስከረም 25/2008 ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች፤ የ26 ሚኒስትሮችና የአራት ካቢኒ ዕጩ አባላትን ለምክር ቤቱ አቅርበው ሹመታቸው በሙሉ የጸደቀበት ዕለት ነበር።

በመንግሥት ምስረታው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የመዋቅር ሽግሽግ በስፋት ተከናውኗል። 12 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የመዋቅር ማሻሻያ ተደርጐባቸዋል፤ ግማሾቹ ሁለት ቦታ እንዲከፈሉ ሲደረግ በአዲስ መልክ የተቋቋሙም ነበሩ።

የፌዴራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስቴር፣ የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር፣ የእንስሳትና የዓሣ ሃብት ልማት ሚኒስቴር እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለውጥ ከተደረገባቸው እና እንደ አዲስ ከተቋቋሙት መካከል ይጠቀሳሉ።

አቶ ደመቀ መኮንን በምክትል ጠቅላይ ሚንስትርነትና የማኅበራዊ ጉዳይ አስተባባሪነት፤ ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነት፣ እንዲሁም ወ/ሮ አስቴር ማሞ በመልካም አስተዳደርና ሪፎርም ክላስተር አስተባባሪና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙት መካከል ይጠቀሳሉ።

ከዓመት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተጨማሪ ሹመቶች በሚኒስትር ማዕረግ ሰጥተዋል። አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እና ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ሹመት ከተሰጣቸው መካከል ናቸው።

በመስከረም 2008 ዓ.ም ካቢኔያቸውን መሥርተው የሥልጣን ዘመናቸውን የጀመሩት አቶ ኃይለ ማርያም ከጥቂት ወራት በኋላ ከመሬት አስተዳደርና ከማንነት ጉዳዮች ጋር የተያያዙ መሰናክሎች ገጥሟቸው።

የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ያዘለ ተቃውሞ ሲቀሰቀስ፣ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደግሞ፣ ከቅማንት የማንነት ጥያቄ አለመመለስ ጋር ተያይዞ ደም ያፈሰሰና የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ግጭት ተቀስቅሶ ነበር።

ለዚህ የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መንግሥት ጥልቅ ተሃድሶ አደርጋለሁ ብሎ ገለጸ።

ይህን ተከትሎ ጥቅምት 22/2009 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የ30 የካቢኔ አባላትን ሹመት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ጸደቀላቸው። ከካቢኔ አባላቱ መካከል 21ዱ አዳዲስ ሲሆኑ 9ኙ ደግሞ ነባር አባላት ናቸው። ከመካከላቸው ሦስት ሴቶች ይገኙበታል።

ከዚህ ቀደም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ በክላስተር የማስፈፀም እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሚባሉ ቦታዎች ሙሉ በሙሉ እንዲቀሩ ተደረጉ።

ወቅቱ መንግሥት በአገሪቱ የተከሰተውን ተቃውሞ ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀበት ነው።

በዚህ የካቢኔ ለውጥ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን በመተካት ወርቅነህ ገበየሁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ።

የመንግሥት ኮምዩሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ደግሞ አቶ ጌታቸው ረዳን ተክተዋል።

በነበሩበት ከቀጠሉ ሚኒስትሮች መካከል አቶ ደመቀ መኮንን (ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር)፣ አቶ ሲራጅ ፈርጌሣ (የመከላከያ ሚኒስትር)፣ ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር) እና ዶ/ር ይናገር ደሴ (የብሔራዊ ኘላን ኮሚሽን ኃላፊ ሚኒስትር) ይጠቀሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲሱ ካቢኔያቸው እንዲካተቱ ካደረጓቸው 13 አዳዲስ ሚኒስትሮች ውስጥ አሥሩ በከፍተኛው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተካተው የማያውቁ፣ ይልቁንም በርካታ ጊዜያቸውን በምርምርና በማስተማር ላይ ያሳለፉ ናቸው።

የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ በንግድ ሚኒስትርነት የተሾሙት ዶ/ር በቀለ ቡላዶ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ተደርገው የተሾሙት ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ሂሩት ወልደ ማርያም፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እና ለመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ተጠቃሾች ናቸው።

የካቲት 8/2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኢሕአዴግ ሊቀመንበርነታቸውና ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቀረቡ።

በወቅቱ ከድርጅት መሪነትና ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት "የአገሪቱ ችግር የመፍትሄ አካል ለመሆን" ስለፈለጉ መሆኑንም ገልጸው ነበር።

ሰኞ መጋቢት 24/2010 በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሚያዝያ 11/2010 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳዲስና ነባር ሚኒስትሮችን አቅርበው ሹመታቸው አደቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቀረቧቸው ሚኒስትሮች የቦታ ሽግሽግ ያደረጉና አዳዲስ ሰዎችም ተካተውበታል። የተወሰኑ የቀድሞ ሚኒስትሮች ያልተካተቱ ሲሆን ጌታቸው አምባዬ (ጠቅላይ አቃቤ ህግ)፣ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ (የኮምዩኒኬሽን ሚኒስትር) ይገኙበታል። የቦታ ሽግሽግ ካደረጉት መካከል አቶ ሲራጅ ፈጌሳ እና አቶ ሙቱማ መቃሳ ይገኙበታል።

ሞቱማ መቃሳ (የመከላከያ ሚኒስትር)፣ አቶ አህመድ ሺዴ (በሚኒስትር ማዕረግ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር)፣ ዶ/ር ስለሺ በቀለ (የውሃ፣ መስኖና እና የኤሌክትሪክ ሚኒስትር)፣ ተሾመ ቶጋ (የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር)፣ ዶ/ር አምባቸው መኮንን (የኢንዱስትሪ ሚኒስትር) እና ወርቅነህ ገበየሁ (የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር) ሆነው ተሹመዋል።

አቶ አባዱላ ገመዳ (የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትር)፣ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር (በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ)፣ ዶ/ር በቀለ ቡላዶ (የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር) እና አቶ ተመስገን ጥሩነህ (የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር) ሌሎች በተመሳሳይ ዕለት ሹመት ያገኙ የፌዴራል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች ሆኑ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥቂት ቀናት ልዩነትም ለ43 የፌዴራል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሹመት ሰጡ። ከእነዚህ አብዛኛዎቹ የሚኒስትር ዴኤታዎችን የያዘ ሹመት ነው።

ጥቅምት 6/2011 በተደረገ የካቢኔ ሹመት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአዲሱ ካቢኔያቸው ከሃያዎቹ ሚኒስትሮች አስሩን ሴቶች አድርገው ሾሙ።

ኢንጅነር አይሻ መሃመድ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ ሲሆን በኢትዮጵያ ታሪክም የመጀመሪያዋ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር እንደሆኑ ተገልጿል።

ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አዲስ የተቋቋመውን የሠላም ሚኒስትር ሲመሩ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር፣ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የገቢዎች ሚኒስትር፣ ዶ/ር ሂሩት ወልደማሪያም የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር፣ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ የትራንስፖርት ሚኒስትር፣ ወ/ት የዓለም ፀጋዬ አስፋው የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚኒስትር እንዲሁም ዶ/ር ፍፁም አሰፋ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ሆነው ተሹመዋል።

የሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ቁጥር ከሃያ ስምንት ወደ ሃያ እንዲያንስ የተደረገ ሲሆን ይህም ወጭ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወቅቱ ተናግረዋል።

አቶ ብናልፍ አንዷለም (በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ)፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ (የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር) እና አቶ ደሴ ዳልኬ (በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብርናና የመስኖ አማካሪ) በመሆን ከተሾሙት መካከል ይገኙበታል።

ኅዳር 18/2011 ዓ.ም ተጨማሪ ሹመት ተሰጠ።

ዶ/ር አምባቸው መኮንን (በጠቅላይ ሚንስትሩ የመሠረተ ልማትና የከተማ ልማት አማካሪ ሚንስትር)፣ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ (በጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትር ዴኤታ)፣ ብርጋዴል ጄኔራል አህመድ ሃምዛ (የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር)፣ አቶ ሞቱማ መቃሳ (የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትር ዴኤታ) እና አቶ ከበደ ጫኔ (የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር) ከተሿሚዎች መካከል ናቸው።

ሚያዝያ 14/2011 ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአራት ከፍተኛ አመራሮች ሌላ ሹመት ሰጡ።

በዚሁ መሠረት ዶ/ር አለሙ ስሜ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ ጃንጥራር አባይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሠረተ ልማትና የከተማ ልማት አማካሪ ሚኒስትር፣ ወ/ሮ ጠይባ ሃሰን በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሆነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የካቲት 17/2012 አቶ ዮሐንስ ቧያለውን የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዚዳንት እና ዶ/ር አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማን ደግሞ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አድርገው ሾመው ነበር።

ሹመቱ ቀጥሎ ጥር 13/2012 ዶ/ር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ የትምህርት ሚኒስትር፣ አቶ መላኩ አለበል የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር እና ዶ/ር አብርሃም በላይ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

ሌላው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሹመት ነሐሴ 14/2012 ተሰጠ።

በወቅቱ ከኦሮሚያ የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው የታገዱት አቶ ለማ መገርሳ ከመከላከያ ሚኒስትርነታቸው ተነስተዋል። በምትካቸው ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር) የመከላከያ ሚንስትር ሆነው ተሹመዋል።

በወ/ሮ አዳነች አቤቤ ምትክ ጌድዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግነቱን ቦታ ተረከቡ።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የነበሩት ታከለ ኡማ በማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትርነት እንዲያገለግሉ ተሾሙ።

ተስፋዬ ዳባና ፍቃዱ ፀጋ በምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግነት፣ ዮሐንስ ቧያለው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር፣ እንደአወቅ አብቴ የብረታ ብረት ኢንጅኔሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደ ማርያም በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሆነው ተሾሙ።

የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ቃለ አቀባይ የነበሩት አቶ ንጉሡ ጥላሁን ካሉበት ኃላፊነት ተነስተው የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነርነት ሹመት ተሰጣቸው።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ተጨማሪ ሹም ሽሮችን ጥቅምት 29/2013 አካሄደዋል።

ከሹመቱ ከጥቂት ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የህወሓት አማፂያን በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈፅመዋል ካሉ በኋላ መከላከያው በህወሓት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዛቸውን ተናገሩ።

ሹመቱ መንግስት "የሕግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃ" ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ "በአጭር ጊዜና በብቃት ለመወጣት የተደረገ የአመራር ሽግሽግ" እንደሆነም ተገልጿል።

የጄነራል ሰዓረ መኮንን ህልፈተ ህይወት ተከትሎ የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሆነው የተሾሙት ጄነራል አደም መሐመድ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ምክትላቸው የነበሩት ጄነራል ብርሃኑ ጁላ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሆነዋል።

ጥሪ ተደርጎላቸው የኢትዮጵያን ጦር የተቀላቀሉት ሌተናል ጄነራል አበባው ታደሰ ደግሞ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሆነው ተሾሙ።

የአቶ ተመስገን ጥሩነህን ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት ተነስተው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ አገኘሁ ተሻገር የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሆነዋል።

በሹም ሽሩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ከኃላፊነታቸው ተነስተው በምትካቸው ደመላሽ ገ/ሚካኤል ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል።

ከቀናት በኋላ በሚደረገው የመንግሥት ምሥረታም ቢያንስ ሦስት ሚኒስትሮች ቦታቸውን እንደሚለቁ እርግጥ ሆኗል።

ቀዳሚዋ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ ሲሆኑ በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን መልቀቃቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል።

ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ ከፌደራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ወደ አዲስ አበባ ቢሮዎች የተዛወሩ ናቸው። የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር የነበሩት ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) የአዲስ አበባ የባህል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ፤ የመከላከያ ሚንስትር የነበሩት ያደታ ቀነዓ (ዶ/ር) ደግሞ የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮን እንዲመሩ ተሹመዋል።