ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ 145 ሰዎች በታጣቂዎች መታገታቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከልና ካማሺ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ታጣቂዎች 145 የሚሆኑ ሰዎችን አግተው መያዛቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በአካባቢው ያለውን የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ ከመስከረም 14/2014 ዓ.ም ጀምሮ በነዋሪዎች "የጉሙዝ ታጣቂዎች" የተባሉ ኃይሎች ሕጻናትን፣ ሴቶችንና አረጋውያንን ጨምሮ ወደ 145 የሚገመቱ የጉሙዝ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ቤተሰቦችን ማገታቸውን ከጥቃቱ ካመለጡ ነዋሪዎች መረዳቱን ገልጿል።
ታጣቂዎቹ "ዓላማችንን አልደገፋችሁም" በሚል ምክንያት ነዋሪዎቹን አግተው "መርሻው" እና "ኤክፈት" ተብሎ ወደሚጠራ አካባቢ ወስደው በቁጥጥራቸው ስር እንዳደረጓቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከታጋቾቹ መካከል "ቢያንስ ሁለት ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውን" እንዲሁም ሌሎቹ "በአስከፊ የስቃይ ሁኔታ ውስጥ" መያዛቸውን ኮሚሽኑ መረጃ ማግኘቱን ጠቅሷል።
በክልሉ ውስጥ በተለይም ከጥር ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሴዳል ወረዳ በሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሳቢያ በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ወደሌሎች አካባቢዎች የሸሹ ሲሆን ከመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ መሆናቸውን ነዋሪዎች እንደገለጹለት ኮሚሽኑ አመልክቷል።
መስከረም 14/2014 ዓ.ም የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ወደ አምስት ሺህ የሚሆኑ ተጨማሪ የሴዳል ወረዳ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ለጊዜው በወረዳው መስተዳደር ግቢ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ መሆናቸው ተገልጿል።
ኢሰመኮ ከመስከረም 16/2014 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው በፀጥታ ኃይሎችና በታጣቂዎቹ መካከል "ውጊያ" በመካሄድ ላይ መሆኑንና ከመስከረም 19/2014 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ነዋሪዎችን ወደ ዳሊቲ ከተማ ለማሸሽ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ባደረገው ክትትል መገንዘቡን አመልክቷል።
ነገር ግን በአካባቢው የሚንቀሳቀሱትን ታጣቂ ኃይሎች ለመቆጣጠር የተሰማራው የፀጥታ ኃይል በቂ እንዳልሆነ የሴዳል ወረዳ አመራሮችና ከወረዳው የሸሹ ነዋሪዎች መግለጻቸውን ኢሰመኮ ገልጿል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ክስተቱን በተመለከተ "ታግተው የሚገኙ ነዋሪዎች ለተባባሰ የሰብአዊ ቀውስ እንዳይጋለጡና ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች የሚገኙ ነዋሪዎች አስፈላጊው የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስላቸው አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ" ጠይቀዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል እና ካማሺ ዞኖች ያለውን የፀጥታ ሁኔታና የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ በፌዴራል መንግሥትና በአካባቢው ኮማንድ ፖስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በተሻለ ፍጥነት ሊተገበሩና ሊጠናከሩ እንደሚገባ አሳሰቧል።
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በካማሺ እና በመተከል ዞኖች በተደጋጋሚ በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች የሲቪል ሰዎች ሕይወት፣ አካል እና ንብረት አደጋ ላይ ወድቆ ቢቆይም፣ በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት የተወሰዱት እርምጃዎች በቂ ባለመሆናቸው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሁለንተናዊ መፍትሔ እንዲፈለግ ኮሚሽኑ ጠይቋል።