የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ሳርኮዚ ለምርጫ ቅስቀሳ ባወጡት ወጪ አንድ ዓመት ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የቀድሞ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኒኮላስ ሳርኮዚ ዳግም ለመመረጥ በሕግ ከሚፈቀደው በላይ ለምርጫ ቅስቀሳ ገንዘብ ወጪ አድርገዋል ተብለው የአንድ ዓመት እስር ተፈረደባቸው።
ሳርኮዚ እአአ 2012 ላይ ፈረንሳይን ለሁለተኛ ዙር ለመምራት ዳግም ቢወዳደሩም በምርጫው ሳይሳካላቸው መቅረቱ ይታወሳል።
የ66 ዓመቱ የቀድሞው ፕሬዝደንት ለምርጫ ቅሰቀሳ ከሚፈቀደው በላይ ወጪ አድርገዋል ሲል ፓሪስ የሚገኝ ፍርድ ቤት ዛሬ ብይን ሰጥቷል።
ሳርኮዚ በሕግ ከሚፈቀደው በላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዩሮ ወጪ አድርገዋል ብሏል ፍርድ ቤቱ።
ሳርኮዚ የአንድ ዓመት እስር ቢፈረድባቸውም ፍርዳቸውን በእስር ቤት ሆነ መጨረስ አይጠበቅባቸውም።
የሳርኮዚን እንቅስቃሴ መከታተያ በቀድሞው ፕሬዝደንት እግር ላይ ከታሰረ በኋላ ሳርኮዚ የአንድ ዓመት እስራቸውን በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ማሳለፍ ይችላሉ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
የቀድሞ ፕሬዝደንት ምንም ጥፋት የለብኝም የሚሉ ሲሆን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ይላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሳርኮዚ በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሲባሉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ሳርኮዚ ኅዳር ወር ላይ በሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ነበር።
ሳርኮዚ የአንድ ዓመት እስር በተፈረደባቸው ክስ ላይ ፓርቲያቸው ለምርጫ ቅስቀሳ ከሚፈቀው 22.5 ሚሊዮን ዩሮ እጥፍ ለምርጫ ቅስቀሳ ወጪ አድርጓል ተብሏል።
ፓርቲያቸው ለምርጫ ቅስቀሳ ያወጣውን ወጪ ለመደበቅ የሕዝብ ግንኙነት ተቋም ቀጥሮ ለምርጫ ቅስቀሳ የወጣውን ገንዘብ ለድርጅቱ ክፍያ የተፈጸም አስመስሏል።
የፓሪሱ ፍርድ ቤት ዛሬ በሰጠው ብይን ላይ ምንም እንኳ የቀድሞ ፕሬዝደንት በፓርቲው የተፈጸመውን ማጭበርበር በዝርዝር ሊያውቁ ባይችሉም፤ ለምርጫ ቅስቀሳ በሕግ ከሚፈቀደው በላይ ወጪ ስለመሆኑ እያወቁ ምንም አይነት እርምጃ አልወሰዱም ብሏል።
ሳርኮዚ በቀድሞ ፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦላንዴ እስከተተኩበት ጊዜ ድረስ ከእአአ 2007 እስከ 2012 ድረስ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት በመሆን ለአንድ የስልጣን ዘመን አገልግለዋል።












