ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአፍሪካ አገራት ዓለም አቀፉን የኮቪድ-19 ክትባት ግብ አላሳኩም ተባለ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆታጠር ከ54 የአፍሪካ አገራት ውስጥ ከአጠቃላይ ሕዝባቸው 10 በመቶ የሚሆነውን በመክተብ የዓለም ጤና ድርጅትን ግብ ያሳኩት 14ቱ ብቻ መሆናቸው ተገለጸ።

የዓለም ጤና ድርጅት አገራት ከሕዝባቸው ቢያንስ 10 በመቶውን እንዲከትቡ ያስቀመጠው ጊዜ በፈረንጆቹ የመስከረም ወር መጨረሻ ነው።

ለዚህ ግብ አለመሳካት ዋነኛ ምክንያቱ በአብዛኛው ክትባቱን ለድሃ አገራት ለማሰራጨት የተቋቋመው ኮቫክስ በበቂ መጠን ክትባት ማግኘት ባለመቻሉ ነው።

ሲሸልስ፣ ሞሪሺየስ እና ሞሮኮ ከ40 በመቶ በላይ ሕዝባቸውን በመክተብ በአህጉሪቱ ውስጥ ከፍተኛውን የክትባት መጠን አሳክተዋል ተብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት እነዚህን አገራት ክትባቱን በተሳካ መንገድ ያስሄዱበትንም ምክንያትም አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ ጠንካራ የክትባት መርሃ ግብሮቻቸው፣ በአገራቱ የቆዳ ስፋት እና በሕዝባቸው ብዛት ዝቅተኛነት ምክንያት ነው ብሏል።

ሌሎች ዓለም አቀፋዊ ግቡን ያሳኩት አገራት ደግሞ ቱኒዚያ፣ ኢዋቲኒ፣ ኬፕቨርዴ፣ ቦትስዋና፣ ኮሞሮስ፣ ዚምባብዌ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሪታኒያ፣ ሌሶቶ እና ሩዋንዳ ናቸው።

ነገር ግን በአጠቃላይ በአፍሪካ የተከተበው የሕዝብ ቁጥር ግን ከአጠቃላዩ የአህጉሪቱ ሕዝብ 4 በመቶ ብቻ ሲሆን በአውሮፓ ሕብረት አገራት አሃዙ 60 በመቶው ሕዝብ ተከትቧል።

ኮቫክስ ወደ 300 ሚሊዮን የሚጠጉ የክትባት ብልቃቶችን ለአፍሪካ አገራት ለማድረስ አቅዶ ነበር።

ነገር ግን የበለፀጉ አገራት አብዛኞቹን ክትባቶችን ከገዙ በኋላ አምስት ሚሊዮን ብልቃቶችን ብቻ ነው ማግኘት የተቻለው ተብሏል።