ናይኪ በእስያ የሠራተኞች እጥረት ስለገጠመው የሚያመርታቸው ጫማዎች እንደሚዘገዩ አስታወቀ

ዝነኛው የስፖርት ጫማ እና አልባሳት አምራች ናይኪ ለገበያ የሚያቀርባቸው ጫማዎች ምርት እንደሚዘገይ አስታወቀ።

የጫማ ምርት እና አቅርቦት መስተጓጎል የገጠመው እስያ ውስጥ የሠራተኞች እጥረት ስለተከሰተ እንደሆነ ድርጅቱ ተናግሯል።

ምርቶቹን ከእስያ ወስዶ ወደ ገበያ ለማቅረብ ከጉዞ ጋር የተያያዙ መሰናክሎች እንደገጠሙትም አክሏል።

ከናይኪ በተጨማሪ በአሜሪካ ታዋቂ የሆነው ሸቀጥ አከፋፋይ መደብር ካስኮ የምርት እጥረት እንዳጋጠመው ይፋ አድርጓል።

የካስኮ ደንበኞች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የምርት እጥረት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ ገብተው እንደንጽህና መጠበቂያ ሶፍት ያሉ ቁሳቁሶችን ዳግመኛ ማከማቸት ጀምረዋል። ይህም መደብሩ ውስጥ በቂ የሶፍት እንዲሁም ሌሎች ምርቶች አቅርቦት እንዳይኖር አድርጓል።

የካስኮ ደንበኞች ምርት ያላግባብ ከማከማቸታቸው ባሻገር፤ ካስኮ ምርቶቹን አሜሪካ ውስጥ ላሉት መደብሮቹ ማከፋፈልም አልቻለም።

ናይኪ እና ካስኮ የገጠማቸውን የምርት መስተጓጎል በተመለከተ በቃል አቀባዩቻቸው በኩል ለሕዝቡ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

"ዓለም አቀፍ የምርት አቅርቦት እና ማጓጓዣ የትስስር ሠንሰለት ላይ መስተጓጎል በመግተሙ እኛንም ጎድቶናል" ብሏል ናይኪ።

ቬትናም እና ኢንዶኒዥያ ያሉ የናይኪ መደብሮች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ለኮሮናቫይረስ በተጣለ እገዳ ምክንያት ከቤታቸው መውጣት አልቻሉም።

በቬትናም ብቻ የ10 ሳምንት ምርቶች የተጓተተቱ ሲሆን፤ ከእስያ ወደ ሰሜን አሜሪካ ምርቶቹን ለማጓጓዝ የሚወስደው ጊዜ ከ40 ወደ 80 ሳምንታት ከፍ ብሏል።

ካስኮ በበኩሉ መሠረታዊ በሚባሉ ምርቶች ላይ የግዢ ገደብ ጥሏል። ስለዚህም ሶፍት፣ ውሃ፣ የንጽህና መጠበቂያ እና ሌሎችም ምርቶችን በገፍ መግዛት ከልክሏል።

ካስኮ የገጠመው ሌላው ችግር በቂ አሽከርካሪዎች ማጣት ነው። ምርቶችን ከመጋዘን ወደ መደብሮች ማመላለስ ፈተና ሆኖበታል።

"ምርት ወደብ ላይ ይዘገያል። የኮንቴነር እጥረት አለ። ኮቪድ-19 የምርት ዝውውርን አዘግይቷል። የጥሬ እቃ፣ የሠራተኞች እና የሹፌሮች እጥረትም ተከስቷል" ሲል ካስኮ መግለጫ አውጥቷል።

በወረርሽኙ ምክንያት አምራቾች እና አከፋፋዮችም ሥራቸው ተመሰቃቅሏል። ይህም የአቅርቦት እጥረት እያስከተለ ነው።

የልጆች መጫወቻ የሚሠራው ሀስቦ፣ ዝነኛው የስፖርት አልባሳት እና ጫማ አምራች አዲዳስ እና ሌሎችም ድርጅቶች የሠራተኛ እጥረት እንዲሁም የምርት ማጓጓዣ ውስንነት ገጥሟቸዋል።