ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኦሮሚያ አዲሱ መስተዳደር ተመሰረተ፣ አቶ ሽመልስ ርዕሰ መስተዳደር እንዲሆኑ ተሾሙ
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ) መስከረም 15/2014 ዓ.ም ባካሄደው ጉባኤ አዲሱን የክልሉን መንግሥት ሲያዋቅር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ርዕሰ መስተዳደር አድርጎ ሾመ።
በስድስተኛው ዙር ምርጫ ለክልሉ ምክር ቤት አባልነት የተመረጡ እንደራሴዎች በመጀመሪያ ስብሰባቸው የክልሉን ርዕሰ መስተዳደርን ጨምሮ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች የሚያገለግሉ ግለሰቦችን ሾሟል።
በዚህም መሠረት ወ/ሮ ሰዓዳ አብዱረሃማን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሆነው በምክር ቤቱ ሲመረጡ አቶ ኤሊያስ ኡመታ ደግሞ ምክትል አፈ ጉባዔ ሆነዋል።
ይህንንም ተከትሎ ምክር ቤቱ ባለፉት ዓመታት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን አቶ ሽመልስ አብዲሳን ክልሉን ለቀጣይ አምስት ዓመታት እንዲመሩ ሾሟል።
በምክር ቤቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሆነው የተመረጡት አቶ ሽመልስ ባደረጉት ንግግር በቀጣዮቹ ዓመታት "የኦሮሞ ሕዝብን ወደ አዲስ ምዕራፍ በማሻገር ለውጡን ለማስቀጠል" ቃል ገብተዋል።
ጨምረውም አዲሱ አስተዳደራቸው ቀዳሚ ተግባር የክልሉንም ሆነ የአገሪቱ ሰላም አስተማማኝ ማድረግ መሆኑን አመልክተው በተለያዩ መስኮች በክልሉ ውስጥ ለማከናወን ያቀዷቸውን ተግባራት ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለክልሉ ምክር ቤት ክልሉን በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ በመሆን የሚያገለግሉ የካቢኔ አባላቶቻቸውን አቅርበው እንዲፀድቅላቸው አድርገዋል።
በዚሁ መሠረትም አቶ አወሉ አብዲ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር፣ አቶ ፍቃዱ ተሰማ የክልሉ የመንግሥት ተጠሪ፣ ዶ/ር ግርማ አመንቴ በም/ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ሀብት ክላስተር አስተባባሪ፣ ወ/ሮ መስከረም ደበበ በም/ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገቢዎች ባለሥልጣን ኃላፊ ሆነዋል።
እንዲሁም አቶ አዲሱ አረጋ በም/ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ፣ አቶ አብዱራህማን አብደላ በም/ርዕስ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ፣ አቶ አብዱልሀኪም ሙሉ በም/ርዕስ መስተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪነት ቦታን ይዘዋል።
በተጨማሪም የክልሉን የተለያዩ ቢሮዎች እንዲመሩ 24 ሰዎች በቢሮ ኃላፊነት ሲሾሙ ከመካከላቸው ከዚህ ቀደም በኃላፊነት ላይ የነበሩና አዳዲስ ተሿሚዎች ተካተዋል።
ከዚህ የቢሮ ኃላፊነት ሹመት ውስጥ የክልሉ ገዢ ፓርቲ ከሆነው ብልጽግና ውጪ የሆኑት አቶ አራርሶ ቢቂላ የክልሉ ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሆነው መሾማቸው ታውቋል።
አቶ አራርሶ ቢቂላ በአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተለይተው ከወጡና በግንባሩ ስም የሚንቀሳቀሰውን ወገኖች የሚመሩ ናቸው።
ለቀጣይ አምስት ዓመታት ክልሉን ከሚመራው የካቢኔ ሹመት ውስጥ የአቶ አራርሳ መካተት አንድ የተለየ ክስተት ሆኖ ታይቷል።
ባለፈው ሰኔ ወር በተካሄደው ክልላዊና አገራዊ ምርጫ መሠረት ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያን ጨምሮ ምርጫው በተካሄደባቸው ክልሎች የበላይነት በማግኘት ማሸነፉ ይታወሳል።
አዲሱ ዓመት መግባቱን ተከትሎ ክልሎች መስተዳደሮቻቸውን በአዲስ ለማዋቀር መረሃ ግብር ያወጡ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ቀዳሚው ሆኗል። በሚቀጥለው ሳምንትም ሌሎቹ ክልሎች አዲስ መስተዳደሮቻቸውን ይመሰርታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የፌደራል መንግሥቱ ምክር ቤት ደግሞ ከሳምንት በኋላ መስከረም 24/2014 ዓ.ም አዲሱን መንግሥት ይመሰርታል።