ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተሽከርካሪዎች እጥረት እርዳታ ለማቅረብ እንቅፋት እንደሆነበት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለጸ
በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ ቀውስን ለመፍታት የጭነት ተሽከርካሪዎች እጥረት እንቅፋት እንደሆነበት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለጸ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳለው ከ400 በላይ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች በአማጺያኑ ቁጥጥር ስር ለሚገኙ ሰዎች እርዳታ ለማቅረብ በሄዱበት ሳይመለሱ ቀርተዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ ጌማ ስኖውደን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ድርጅታቸው የእርዳታ ቁሳቁሶችን ወደ ትግራይ እንዲያደርሱ የተከራያቸው የጭነት ተሽከርካሪዎች የት እንዳሉ የሚያውቀው ነገር የለም።
ድርጅቱ እርዳታ ለማድረስ ወደ ትግራይ የሄዱ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች አለመመለሳቸው "እንዳሳሰበው" ቀደም ሲል ገልጾ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ተሽከርካሪዎቹን የትግራይ አማጺያን ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር በሚያደርጉት ጦርነት ውስጥ እየተገለገሉባቸው ሊሆን እንደሚችል አመልክቶ ነበር።
ነገር ግን የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ ተሽከርካሪዎቹ ወደ መጡበት ያልተመለሱት የነዳጅ ችግር ስለገጠማቸው ነው ብለዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጨምሮም በረሃብ ውስጥ ለሚገኙት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እርዳታ ለማቅረብ በጣሙን አስፈላጊ የሆኑት ተሽከርካሪዎች እንዲመለሱ ከትራንስፖርት ድርጅቶችና ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመስራት ፈቃደኛ መሆኑን አመልክቷል።
የተሽከርካሪዎቹ አለመመለስ ያስከተለው ስጋት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ቁሳቁስ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል ከገቡ በኋላ ሳይመለሱ የሚቀሩ ከባድ የጭነት ተሸከርካሪዎች ጉዳይ እንዳሳሰበው ገልጿል።
በኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት ጽህፈት ቤት በትዊተር ገጹ ላይ እንደገለጸው ባለፈው ሳምንት መቀለ ከደረሱ 149 ተሽከርካሪዎች መካከል አንዳቸውም አልተመለሱም።
ከሐምሌ 05/2013 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ትግራይ ክልል የእርዳታ ቁሶችን ይዘው ከገቡ 466 ከባድ የጭነት መኪኖች መካከል 38ቱ ብቻ መመለሳቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።
የተሽከርካሪዎቹ ከክልሉ አለመመለስ ያሳሰበው የመንግሥታቱ ድርጅት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚያስፈልገውን ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ የጭነት ተሽከርካሪዎቹ ያስፈልጉኛል ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ተሽከርካሪዎቹ አለመመለሳቸው እንዳሳሰበው በትዊተር ገጹ ላይ ማስፈሩን ተከትሎ የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ እዚያው ላይ ምላሽ ሰጥተዋል።
አቶ ጌታቸው የድርጅቱን ስጋት እንደሚጋሩ በመጥቀስ "አሽከርካሪዎቹ የነዳጅ ችግር፣ የደኅንነት ስጋት፣ በፍተሻ ጣቢያዎች ላይ የሚደርሱ መጉላላቶች፣ ለወራት አፋር ውስጥ መቆማቸውን" ላለመመለሳቸው ምክንያት መሆኑን በመጥቀስ ምክንያት ያሉትን አስፍረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት
በተመሳሳይ የመንግሥታቱ ድርጅት ያጋጠመውን ከመግለጹ ቀደም ብሎ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ሐሙስ መስከረም 06/2014 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ትግራይ ከገቡ ተሸከርካሪዎች 428ቱ ከክልሉ አለመውጣቸው ገልጸዋል።
በተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አማካኝነት ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁሶችን የጫኑ 590 ከባድ ተሽከርካሪዎች ከሰመራ ወደ መቀለ መጓጓዛቸውን ቢልለኔ ተናግረዋል።
በአንድ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት አማካኝነት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲያደርሱ ከገቡ 466 ከባድ የጭነት ተሸከርካሪዎች መካከል 428 የሚሆኑት እስካሁን ከክልሉ አለመውጣታቸውን አስረድተዋል።
ቢልለኔ መግለጫቸው ከክልሉ ሳይወጡ የቀሩት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎቹ በክልሉ ውስጥ ለምን አገልግሎት እየዋሉ እንደሆነ ግልጽ ባለመሆኑ በመንግሥት ዘንድ ጥርጣሬን መፍጠሩን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የሰላም ሚኒስቴር ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ ጭነው የገቡ ተሸከርካሪዎች በተቀመጠው የአሰራር ሥርዓት መሠረት ተመልሰው መውጣት ሲገባቸው አለመመለሳቸው ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ እና ጥርጣሬ እንዲፈጠር እንዳደረገ ገልጾ ነበር።
ሚኒስቴሩ፤ "በተጨባጭ ከአላማቸው [ተሸከርካሪዎቹ] ውጪ ተሰማርተው ላለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሰጥ አካል አልተገኘም" ብሎ ነበር ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ላይ።
ቢልለኔ ወደ ትግራይ የሚደረጉ የአየር እና የየብስ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ጉዞዎች እንደቀጠሉ መሆናቸውን አመልክተው፤ የአውሮፓ ሕብረት የሰብዓዊ እርዳታ በረራም ከአንድ ሳምንት በፊት መጀመሩን ተናግረዋል።
እስከ መስከረም 04/2014 ዓ.ም. ድረስ 32 ተቋማት ለሰብዓዊ ሥራቸው 144 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ወደ መቀለ መውሰዳቸውንም ጠቅሰዋል።
ከምግብ ውጪ፤ ወደ 760 ሺህ ሊትር የሚጠጋ ነዳጅ እና ከ1ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የግብርና ግብዓቶች ወደ ክልሉ መጓጓዙን አመላክተዋል።
እስከ መስከረም 4 ድረስ እንቅስቃሴያቸው ተስተጓጉሎ የቆሙ ተሸከርካሪዎች የሉም ያሉት ብልለኔ፤ መንግሥት የእርዳታ ቁሳቁሶች ወደ ክልሉ በፍጥነት እንዲገቡ ለማቀላጠፍ ሰባት የነበሩትን የፍተሻ ጣቢያዎች ወደ ሁለት ቀንሷል ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ትግራይ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በረሃብ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የእርዳታ ድርጅቶች አስታውቀዋል።
ትግራይ ውስጥ ከተቀሰቀሰ ከአስር ወራት በላይ የሆነው ጦርነት ወደ አጎራባች የአማራና የአፋር ክልሎች የተስፋፋ ሲሆን ከባድ ሰብዓዊ ቀውስን አስከትሏል። በዚህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ በአማራ ክልል
ቃል አቀባይዋ ጨማረውም በአማራ እና በአፋር ክልል በህወሓት አማጺያን ጥቃት ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ በርካታ ዜጎች አሉ ብለዋል።
በአማራ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ500 ሺህ መሻገሩን እና አብዛኛው ሕዝብ የተፈናቀለው ከዋግ ኽምራ፣ ከሠሜን ጎንደር፣ ከደቡብ ጎንደር፣ ከሠሜን ወሎ እና ከደቡብ ወሎ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሠሜን ወሎ ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ተጠልለው የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ወደ 270ሺህ እንደሚጠጋም አመልክተዋል።
ከቀያቸው ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለሚገኙ ዜጎች መንግሥት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን እስከ መስከረም 4/2014 ድረስ 27ሺህ ኩንታል እህል አቅርቧል። 2600 በላይ ኩንታል እህል ደግሞ በዋግ ኽምራ ዞን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ተልኳል።
ይሁን እንጂ በህወሓት አማጺያን ቁጥጥር ሥር በሚገኙ የሠሜን ወሎ ወረዳዎች የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶችን ማቅረብ አልተቻለም ብለዋል ቢልለኔ።
ወትሮም ቢሆን የምግብ እጥረት ባለበት ሠሜን ወሎ፤ ህወሓት የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች እርዳታ እንዳያደርሱ እክል መሆኑ ሁኔታዎችን ያባብሳል ብለዋል።
መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለትግራይ ክልል የሰጡትን ትኩረት ለአማራ እና ለአፋር ክልል ተጎጂዎችም እንዲሰጡ መንግሥት ማሳሰቡንም ተናግረዋል።