የአፍሪካ ሕብረት ትግራይ ውስጥ ረሃብ እንዳይከሰት የእርዳታ አቅርቦት እንዲቀላጠፍ ጠየቀ

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ረሃብ እንዳይከሰት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት የተቀላጠፈ እንዲሆን የአፍሪካ ሕብረት ጠየቀ።

የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ አንድ የሕብረቱን ከፍተኛ ባለሥልጣን ጠቅሶ እንደዘገበው የእርዳታ ሠራተኞች እርዳታ የሚሹ ሰዎችን ለመድረስ በተቸገሩበት ወቅት መንግሥት እርዳታን ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር የሆኑት ባንኮሌ አዶዬ "የኢትዮጵያ መንግሥት የሚችለውን እያደረገ መሆኑን፤ ነገር ግን ሰዎች እንዳይራቡ የበለጠ እንዲሰራ እንፈልጋለን" ሲሉ አርብ ዕለት መናገራቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ጨምረውም "ሴቶችና ህጻናት የእነሱ ባልሆነ ግጭት ውስጥ ሰለባ ሆነው መቀጠል የለባቸውም" ሲሉ ባለሥልጣኑ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ በትግራይ ክልል ካለው 90 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገውና 400 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በረሃብ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጿል።

ሐሙስ ዕለት የማስተባበሪያው ኃላፊ በክልሉ ውስጥ የነበረው የእርዳታ አቅርቦት ከተጠናቀቀ ሁለት ሳምንት እንደሆነው አስታውቀዋል።

በተጨማሪም አስፈላጊ የሆኑ የሰብዓዊ እርዳታዎችን ማቅረብ አለመቻሉ፣ የነዳጅ እና የጥሬ ገንዘብ እጥረት መኖሩ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በትግራይ ክልል ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ከትግራይ ክልል በተጨማሪ በአጎራባቾቹ አማራ እና የአፋር ክልሎች ውስጥ ደግሞ 1.7 ሚሊዮን ሕዝብ ለረሃብ ሊጋለጡ ከጫፍ ደርሰዋል ሲሉ የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪው ግራንት ሌይቲ አመልክተዋል።

ኃላፊው በትግራይ ክልል ውስጥ የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ የሚቻልበት ሁኔታ ቢኖርም እንዲሁም የደኅንነት ሁኔታው ቢሻሻልም ክልሉ "ይፋ ባልሆነ የሰብዓዊ እርዳታ እቀባ ስር ይገኛል" ብለዋል።

የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መጓተትን በተመለከተ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ቢል ለኔ ስዩም በሰጡት ማብራሪያ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ ለማድረስ እንቅፋት ናቸው የተባሉ አሠራሮች እንዲስተካከሉ ማድረጉን ገልጸዋል።

ጨምረውም እርዳታ በተገቢው ሁኔታ እንዳይቀርብ "እንቅፋት እየፈጠረ ያለው ህወሓት በመሆኑ የተደራሽነት ችግር ጥያቄ መነሳት ያለበት ከዚሁ ቡድን አንጻር ነው" ብለዋል ።

ለወራት በትግራይ ክልል ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተስፋፋ ሲሆን እዚያም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ለችግር የተጋለጡትን ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ተዘግቧል።

የአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር የሆኑት ባንኮሌ አዶዬ የእርዳታ አቅርቦት እንዲጠናከር ከመጠየቃቸው በተጨማሪ "ወታደራዊ መፍትሔ አዋጪ ባለመሆኑ" በጦርነቱ ውስጥ ያሉ ሁለቱም ወገኖች "ወደ ድርድር ጠረጴዛ" እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

አሁንም በተለያዩ የአማራና የአፋር አካባቢዎች በፌደራል መንግሥቱ የሚመሩት የአገሪቱ ሠራዊት፣ የክልሎች ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ከህወሓት ኃይሎች ጋር የሚያደርጉት ውጊያ እንደቀጠለ ነው።

ባለፈው ሳምንት የአፍሪካ ሕብረት በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆም መፍትሔ እንዲያፈላልጉ የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን በልዩ መልዕክተኝነት መሾሙ ይታወሳል።