ሰሜን ኮሪያ በድጋሚ የኒኩሌር ማብላያዋን ስራ ማስጀመሯ ተገለጸ

ሰሜን ኮሪያ የኒኩሌር ማብላያዋን በድጋሚ ወደስራ እንዳስገባች የተባበሩት መንግስታት የአቶሚክ ኤጀንሲ ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።

ለኒኩሌር የጦር መሣሪያ የሚያገለግለው ፕሉቶኒየም የተሰኘውን ንጥረ ነገር በዚሁ መብላያዋ ውስጥ እያበለጸገች እንደሚትገኝ ሪፖርቱ አክሏል።

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ከፒዮንግያንግ እኤአ በ2009 የተባረረ ቢሆንም ክትትሎቹን እና ምርመራዎቹን በሳተላይት ምስሎች ላይ ተመስርቶ እያካሄደ ይገኛል።

ተቋሙ እንዳመለከተው ማብላያው ካለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ የማቀዝቀዣ ውሃ እያስወገደ ሲሆን ይህም ስራ መጀመሩን የሚጠቁም ነው።

ዮንግቦን የተሰኘው ይህ የሰሜን ኮሪያ ወሳኝ የኒኩለር ማብላያ አምስት ሜጋ ዋት የሚያመነጭ የኃይል ማመንጫ ይዟል።

ይህ የኒኩሌር ማብላላት እንቅስቃሴም እአአ በ 2018 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ኪም ጆንግ ኡን በሲንጋፖር ከተገናኙ በኋላ የመጀመሪያው እንደሆነም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ባለሙያዎች የዮንግቦን ማመንጫ በውስጡ ምን ያህል የጦር መሣሪያዎችን ማምረት እንደሚችል ለመረዳት ሲከታተሉት ቆይተዋል።

ኤጀንሲው አክሎም የኒኩሌር ነዳጅን እንደገና በጥቅም ላይ ለማዋል የሚረዳውን የራዲዮ ኬሚካል ላቦራቶሪን የተመለከቱ ተጨማሪ መረጃዎችንም ይፋ አድርጓል። ባለፈው ሰኔ ወርም የዚህን ላቦራቶሪ ሥራ መጀመር መጠቆሙ ይታወሳል።

ኤጀንሲው አዲስ ባወጣቅ በዚሁ ሪፖርት ውስጥም ላቦራቶሪው እስከ ሐምሌ 2021 ድረስ ለአምስት ወራት ሲሠራ የቆየ ሲሆን ይህም በሙሉ አቅሙ ይሀንኑን ጥቅም ላይ የዋለ ነዳጅ ላይ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አመላክቷል።

ኤጀንሲው አክሎም በኒኩሌር ማብላያው ብሎም በላቦራቶሪዉ እየተካሄዱ ያሉ ሁኔታዎች እጅግ አሳሳቢ እና የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎችን በግልፅ የሚጥሱ መሆናቸውን ገልጿል።

የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዮናፕ የዜና ወኪል እንደገለፀው መንግሥት "ከአሜሪካ ጋር በቅርበት በመተባበር የሰሜን ኑኩሌር እና ሚሳይል እንቅስቃሴዎችን በተከታታይ እየተከታተለ ነው"።