አይ ኤስ በካቡል ጥቃት ሊሰነዝር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላት አሜሪካ ገለጸች

የአሜሪካ ኃይል

የፎቶው ባለመብት, US Marine Corps/Reuters

አይ ኤስ በካቡል አየር ማረፊያ ላይ ጥቃት ሊሰነዝር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላት አሜሪካ ገለጸች

በአፍጋኒስታን የሚንቀሳቀሰው የኢስላሚክ ስቴት(አይኤስ) ቡድን ጥቃት ሊያደርስ ይችላል በሚል ስጋት አሜሪካ ዜጎቿ ከካቡል አውሮፕላን ማረፊያ እንዲርቁ አስጠነቀቀች።

ቅዳሜ ዕለት በተሰራጨ አንድ የደህንነት ማስጠንቀቂያ የአሜሪካ ዜጎች "ከመግቢያዎች ውጪ ባለው የደህንነት ስጋት" ምክንያት ራሳቸውን ከአደጋ እንዲያርቁ ተነግሯቸዋል።

በአሜሪካ መንግስት ተወካይ ጉዞ እንዲያደርጉ በግል የተነገራቸው ሰዎች ብቻ ናቸው ወደ ኤርፖርት ማቅናት የሚችሉትም ተብሏል።

የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣናት በአፍጋኒስታን ያሉ ሁኔታዎችን እየተከታተሉ እና አማራጭ መንገዶችን እያጤኑ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።

አይ ኤስ ሊሰነዝርው ይችላል ስለተባለው ጥቃት ዝርዝር መግለጫ አልተሰጠም። ቡድኑም በካቡል ጥቃቶችን ለመፈጸም በይፋ አልዛተም።

ታሊባንን አፍጋኒስታንን መቆጣጠሩን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሀገሪቱን ጥለው ለመሸሽ ሲሞክሩ ከካቡል ከኤርፖርቱ ተርሚናል ውጭ በተፈጠረው ሁከት ለጉዳት መዳረጋቸውን በቅዳሜው የአሜሪካ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ተጠቅሷል።

ታሊባን ባለፈው ሳምንት አፍጋኒስታንን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር የሀገሪቱን ስልጣን በዕጁ እንዳስገባ የሚታወስ ነው።

ከሀገሪቱ የሚወጡባቸውን በረራ እንደሚገኙ ተስፋ በማድረግ በካቡል ኤርፖርት አቅራቢያ በርካታ ሰዎች በየቀኑ ይሰባሰባሉ። ከአሜሪካ እና ከአጋሮቿ ጋር የሚሰሩ እንዲሁም እንደ ሰብአዊ መብቶች ባሉ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የነበራቸው ሰዎች በሀገሪቱ ቢቆዩ በታሊባን እጅ የበቀል እርምጃ ይደርስብናል የሚል ስጋት አላቸው።