የዶ/ር ቴድሮስን ዳግም መመረጥ የሚቃወመው ድርጅት ቀጣዩ ምርጫ ግልጽ እንዲሆን ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ዳግም መመረጥ የሚቃወመው ድርጅት ቀጣዩ ምርጫ ግልጽ በሆነ መልኩ መካሄድ አለበት ሲል ጠየቀ።
ኤድስ ሔልዝኬር ፋውንዴሽን (ኤኤችኤፍ) የተባለው ድርጅት የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን በአንድ ወር ውስጥ ማቅረብ እንደሚጀምሩ አስታውሶ፤ ምርጫው ግልጽነት ሊኖረው ይገባል ብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ምርጫ "ግልጽ፣ ፍትሃዊ፣ ችሎታ ላይ መሠረት ያደረገ እና የተለያየ ዳራ ያላቸው በዕጩነት የሚቀርቡበት" መሆን አለበት ይላል ኤኤችኤፍ።
"ወረርሽኙን በግልጽ መቆጣጠር ያልቻሉትን ዶ/ር ቴድሮስን ማን ይተካቸዋል ነው ጥያቄው፤ ምርጫው ግልጽ መሆን አለበት" ሲሉ ኤኤችኤፍ ፕሬዝደንት ማይክል ዌኒስቲን ተናግረዋል።
ኤድስ ሔልዝኬር ፋውንዴሽን (ኤኤችኤፍ) የዓለማችን ግዙፉ በኤድስ ጉዳይ የሚሳራ ድርጅት ነው።
ኤኤችኤፍ በአሁኑ ወቅት በ45 አገራት ለሚገኙ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች የሕክምና አገልግሎት እና እንክብካቤ እንደሚሰጥ ይገልጻል።
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለሁለተኛ ዙር የዓለም ጤና ድርጅትን በዋና ዳይሬክተር ማዕረግ ለአምስት ዓመታት ዳግም ለመምራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን በማስታወስ፤ ኤኤችኤፍ ሰኔ አጋማሽ ላይ ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅትን ለመምራት ዳግም መመረጥ የለባቸውም ያላቸውን ምክንያቶች ዘርዝሮ ነበር።
በዋናነት የተቀመጠው ምክንያት ዶ/ር ቴድሮስ የሚመሩት የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19ን የሕዝብ የጤና አደጋ በማለት በፍጥነት አልፈረጀም እንዲሁም ኮቪድ-19ን "ወረርሽኝ ብሎ" ለመፈረጅ ዘግይቷል የሚለው ይገኝበታል።
ከዚህ በተጨማሪም የኮቪድ-19 መነሻ ግልጽነት አለመኖሩ እና ለወረርሽኙ ክትባቶችን በፍጥነት አለማጽደቅ ድርጅቱ ዶ/ር ቴድሮስን ከተቸባቸው ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።
ኤኤችኤፍ በቀጣዩ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ምርጫ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት ለመሙላት የዕጩዎች ምርጫን ግልጽ እና ሁሉን አካታች ማድረግ አለባቸው ብሏል።
ለረዥም ጊዜ የኢትዮጵያ ጤና ሚንስቴር ሚንስትር እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም እአአ 2017 ላይ ነበር የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ተብለው የተሾሙት።
የዓለም ጤና ድርጅት መሪ ምርጫ የሚከናወነው እንዴት ነው?
የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ዕጩዎቻቸውን ለየዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ያቀርባሉ።
ቦርዱ ከአባል አገራቱ የቀረቡለትን ዕጩዎች በሙሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት አምስት ዕጩዎችን ይዘረዝራል።
ቦርዱ በመቀጠል ከአምስቱ ዕጩዎች የመጨረሻዎቹን ሦስት ዕጩዎች ለማጠቃለያው ምርጫ ይፋ ያደርጋል።
በመጨረሻም የዓለም ጤና ድርጅት ጉባኤ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርን ይመርጣል።
የፊታችን መስከረም አጋማሽ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አምስቱን ዕጩዎች ይለያል ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚያ በኋላ ደግሞ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የዓለም ጤና ድርጅትን የሚመራው ግለሰብ በሚቀጥለው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ይፋ ይሆናል።
















