ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአፍጋኒስታን ሚኒስትሮች 'ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር' ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ተገለፀ
የታሊባን ኃይሎች የካቡል ከተማን በተለያዩ መግቢያዎች መክበባቸውን ተከትሎ የአፍጋኒስታን ሚኒስትሮች ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
የአፍጋኒስታን የሃገር ውሰጥ ጉዳይ ሚኒስትር በአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቀርበው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንደሚደረግና ለሽግግር መንግሥቱም ስልጣን ይሰጣል በማለትም ካቡል ላይ ጥቃት እንደማይፈፀም ገልጸዋል።የታሊባን ተደራዳሪዎች የስልጣን ሽግግሩ ላይ ለመዘጋጀት ወደ አገሪቱ ፕሬዚዳንት ቢሮ እያመሩ ነው ተብሏል።
የታሊባን ታጣቂዎች በመዲናዋ መውጪያና መግቢያዎች ላይ ታጣቂዎቻቸው እንዲጠብቁ ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር።
ታሊባኖች አፍጋኒስታንን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የተቃረቡ ሲሆን ዋና ከተማዋ ካቡል ብቻ በመንግሥት ስር ያለች ብቸኛዋ ከተማ ሆናለች።
የታሊባን ታጣቂዎቹ ያለምንም ውጊያ በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል የምትገኝ ጃላላባድን የተሰኘችውን ወሳኝ ከተማ ተቆጣጥረዋል።
ታጣቂዎቹ ይህችን ከተማ ከመቆጠጠራቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ የሀገሪቱ ሰሜናዊ የመንግሥት አስተዳደር ዋና መቀመጫ የነበረችውን ማዛር-ኢ-ሻሪፍ በእጃቸው አስገብተው ነበር።
የመንግሥት ኃይሎች በፍጥነት መሸነፍ የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ከፍተኛ ጫና እያስከተለባቸው መሆኑኑም ተሰምቷል።
እናም ፕሬዝዳንቱ ወደ ዋና ከተማዋ እጅግ ከቀረቡት የታሊባንን ታጣቂዎች ጋር በሚደረግ ውጊያ መሳተፍ ወይም ራሳቸውን አሳልፈው መስጠት በሚል አጣብቂኝ ውስጥ መውደቃቸውም ተነግሯል።
አሜሪካ በአፍጋን የሚገኙ ዜጎቿን ለማስወጣት 5 ሺህ ወታደሮች እያሰማራች ነው።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን "በሌላ ሀገር የእርስ በእርስ ግጭት መሃል" ማብቂያው በማይታወቅ ሁኔታ የአሜሪካን መኖር ምክንያታዊ ሊሆን አይችልም ሲሉ የአሜሪካን ጦር ከአፍጋኒስታን የማስወጣት ውሳኔን ትክክለኝነትን አብራርተዋል።