ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የቴሌኮም አገልግሎት ፍቃድ ጨረታ ልታወጣ ነው
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የቴሌኮም ፈቃድ ጨረታ በቀጣዩ ወር እንደምታወጣ ሮይተርስ ሁለት ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
በጨረታው የሚወጣው የአገልግሎት ፈቃድ የሞባይል ገንዘብ መገበያያን እንዲጨምር መደረጉም ተነግሯል።
ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እንደምታደርግ ካሳወቀች በኋላ ሁለት ፈቃዶችን ለዘርፉ ተሳታፊዎች በጨረታ ማቅረቧን ተከትሎ ሁለት ተቋማት በጨረታው ተሳታፊ መሆናቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል።
በዚህም መሠረት የተለያዩ ኩባንያዎች ጥምረት የሆነው ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተባለው ተቋም ከፍተኛውን 850 ሚሊዮን ዶላር በማቅረብ በጨረታው ተመራጭ ሲሆን ሁለተኛው ፈቃድ ሳይሰጥ ቀርቷል።
ለሁለተኛው ፈቃድ ሳይሰጥ የቀረው የቀረበው ዋጋ ከተጠበቀው በታች በመቅረቡ ሲሆን ጨረታው በአሁኑ ወቅት ለሁለተኛ ጊዜ ተሻሽሎም ቀርቧል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ ለሮይተርስ እንደገለፁት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎቹ ለጨረታው የሚያቀርቡትን ዋጋ ለማሳደግ አንዳንድ ለውጦች ተደርገዋል።
ዳይሬክተሩ እንደ ምሳሌም የጠቀሱት የሞባይል የገንዘብ አገልግሎትን ነው።
የዓለም ባንክ የግሉ ዘርፍ ክንድ የሆነው ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን በስምምነቱ የግብይት አማካሪ ሆኖ እንደሚያገለግል በገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ብሩክ ታዬ መናገራቸውም ተዘግቧል።
አማካሪው በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ፈቃዱን ለመግዛት ፍላጎት ያሳዩ ነገር ግን በቂ አይደለም የተባሉ ድርጅቶችም በዚህ ጨረታ ይሳተፋሉ ብሎ መንግሥት እንደሚጠብቅም ተናግረዋል።
አክለውም "ጠንካራ ፍላጎት ይኖራል ብለን እንጠብቃለን" ብለዋል።
በኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ቴሌኮምን ፈቃድ ያሸነፈ ሲሆን በቀጣዮቹ ወራትም ሥራ እንደሚጀምር አስታውቋል።
ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተሰኘው ይህ የኩባንያዎች ጥምረት በዘርፉ አሉ የሚባሉ ስመ ጥር የቴሌኮም ኩባንያዎችንና ተቋማትን በቅንጅት የያዘ ሲሆን እነዚህም ሳፋሪኮም፣ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕና ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽንና ሲዲሲ ግሩፕ ናቸው።
ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ገቢው ትርፋማ ከሚባሉ ድርጅቶች አንዱ ቢሆንም ከሌሎች የቀጠናው ኩባንያዎች ጋር ሲወዳዳር ዝቅተኛ ነው ይላሉ በዘርፉ ያሉ ተንታኞች።
ኢትዮጵያ ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ድርሻ ለመሸጥ የወሰነችው በዋነኝነት ያላትን ከፍተኛ ዕዳ ለመክፈል እንደሆነ ተንታኞች የሚናገሩ ሲሆን፤ በተጨማሪነት የቴሌኮምን ተደራሽነት ለመጨመርና አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ እንደሆነም ይጠቀሳል።
ኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድን ለመስጠት ወደ ገበያው መግባት የሚሹ ፍላጎታቸውን እንዲገልጹ ሲጠየቅ 12 የቴሌኮም ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ውስጥ ለመሳተፍ ፍለጎት እንዳላቸው የገለጹ ቢሆንም የፈረንሳዩን ኦሬንጅ፣ ሳዑዲ ቴሌኮም ኩባንያ፣ ሊኩዊድ ቴሌኮም፣ እንዲሁም የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ኢቲሳላትን ጨምሮ ሌሎችም በጨረታው ላይ ሳይሳተፉ ቀርተዋል።
ሁለተኛ ተጫራች የነበሩት የደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን እና አጋሩ የቻይና መንግሥት ኢንቨስትመንት አካል የሆነው ሲልክ ሮድ ፈንድ 600 ሚሊዮን ዶላር ለጨረታው ያቀረቡ ቢሆንም ሳይመረጥ ቀርቷል።
በዚህም ሳቢያ ሁለተኛው የቴሌኮም ዘርፍ አዲስ ፈቃድ ሳይሰጥ ቢቀርም በቀጣይ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ለጨረታ እንደሚቀርብ ተነግሮ ነበር።
በውጭ ኩባንያዎች ከሚያዙት ሁለቱ የቴሌኮም ፈቃዶች በተጨማሪ ዋነኛው የአገሪቱ አገልግሎት ሰጪ ኢትዮ ቴሌኮምም በሩን ለባለሀብቶች ይከፍታል።
በዚህም በመንግሥት ብቸኛ ባለቤትነት ሥር የቆየው ተቋሙ በቅርቡ 40 በመቶ ድርሻውን ለውጪ ባለሀብቶች፣ 5 በመቶውን ለኢትዮጵያውያን እና 55 በመቶውን መንግሥት እንደሚይዘው ይጠበቃል።