የሆንዱራስ የግድብ ኃላፊ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቿን በማስገደል ጥፋተኛ ተባሉ

የሆንዱራስ ፍርድ ቤት በአውሮፓውያኑ 2016 የተገደለችው ታዋቂዋ የአካባቢ ጥበቃ መብት ተሟጋች ግድያ የቀድሞ የግድብ ስራ አስኪያጅ ጥፋተኛ ናቸው አለ።

በርታ ካሴሬስ የተባለችው የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች አጉዋ ዛርካ የተባለው ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን ትመራ የነበረ ሲሆን በቤቷም በጥይት ነው የተገደለችው።

በፍርድ ቤቱ ብያኔ መሰረት ሮበርቶ ዴቪድ ካስቲሎ የተባሉትና የግድቡን ጨረታ ያሸነፈው ኩባንያ ኃላፊ የተሟጋቿን ግድያ እንዳቀናበሩና ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይም እንደቀጠሩም ተገልጿል።

ካስቲሎ በበኩላቸው ምንም ጥፋት አልሰራሁም ብለዋል። የእስር ጊዜያቸው በነሐሴ ወር የሚወሰን ይሆናል።

በተሟጋቿ ግድያ ሰባት ሰዎች ተሳትፈዋል በሚልም ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ሲሆን ረዘም ያለ እስር ጊዜም ተብይኖባቸዋል።

በርታ ካሴሬስ የግድቡን ፕሮጀክት በበላይነት ሲሰራ የነበረው ደሳ የተባለው የካስቲሎ ኩባንያ ላይ ተቃውሞ በማሰማታቸው ምክንያት ለአመታት ያህል ማስፈራሪያዎች ይደርስባቸው ነበር።

ግድቡ ሌንካ ለተባሉት ቀደምት ህዝቦች መሬታቸውን በጎርፍ ማጥለቅለቅ፣ የውሃ አቅርቦታቸውን መቁረጥ እንዲሁም የምግብና የመድኃኒት አቅርቦታቸውም ላይ ከፍተኛ እክል ፈጥሯል ተብሏል።

ተሟጋቿ ቅሬታቸውንም ይፋዊ በሆነ መልኩ በማቅረብ የግድቡ ሰራተኞች ስፍራው ላይ እንዳይደርሱ በማለት መንገድም ዘግተው ነበር።

በፕሮጀክቱ ላይ ተሳታፊ የነበረው የቻይናው ሲኖሃይድሮ የማህበረሰቡን ተቃውሞ በማየት ራሱን ከግንባታው እንዳገለለ አስታውቋል።

የግድቡን ግንባታ በማስቆም ላይ በነበራት ሚና ተሟጋቿ በአውሮፓውያኑ 2015 ታዋቂ የሆነውን ጎልድማን ፕራይዝ ሽልማት አሸንፋለች።

በርታ ያቋቋመችው የቀደምት ህዝቦች ድርጅትም ውሳኔውን ለሆንዱራስ ህዝብ ድል ብሎታል።

ሆንዱራስ ለአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች በአለም ላይ አደገኛ ከሚባሉ ስፍራዎች እንደሆነ አድቮኬሲ ግሩፕ ግሎባል ዊትነስ የተባለ ድርጅት አስታውቋል።

በርታ ከሞተች በኋላ ቢያንስ 40 የመሬትና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ተገድለዋል።